ዞኑ በግንባር ለሚፋለሙ የጸጥታ ሀይሎች የ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የስንቅ ድጋፍ አደረገ

61

እንጅባራ ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) የአዊ ብሔረሰብ ዞን በዋግ ኽምራ ግንባር የአሸባሪው ህወሓት ወራሪን እየተፋለሙ ላሉ የጸጥታ ሀይሎች 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የስንቅ ድጋፍ አደረገ።

በዞኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከወረዳዎችና ክፍለ ከተማ የተሰባሰበው ደረቅ ስንቅ ትናንት ለሠራዊቱ ተልኳል።  

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በወቅቱ እንዳሉት በጠቅላይ ሚንስትሩ የግንባር አመራር ሰጪነት የተለያዩ አካባቢዎች ከወራሪው ሀይል ነጻ መውጣታቸው በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል።

"ድሉ ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው የሚያደርገውን የደጀንነት ድጋፍ እንዲያጠናክር ከማድረጉ በተጨማሪ ወጣቱ መከላከያን ለመቀላቀል እንዲነሳሳ አድርጎታል" ብለዋል።

የህልውና ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የደረቅ ምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ መበርከቱን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ህዳር ወር 2014 ዓም በተካሄደ 3ኛ ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ደረቅ ስንቅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስና የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የዞኑ ህብረተሰብ የድርሻውን እንደሚወጣ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

በሠላም ቀጠና ያለው ህብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ድጋፉን በማጠናከር የወገን አጋርነቱን ይበልጥ እንዲያሳይ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

በዞኑ የአዲስ ቅዳም ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሎጂስቲክስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ጽጌረዳ አበበ በበኩላቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ ከ800 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ደረቅ ስንቅ ተዘጋጅቶ መላኩን ተናግረዋል።

አገርን ከነሙሉ ክብሯ ጠብቆ ለማቆየት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አረጋግጠዋል።

"በወረዳችን 428 ኩንታል ደረቅ ስንቅ ተዘጋጅቶ ወደ ግንባር መላኩ ለሠራዊቱ ሞራልና ለድሉ ቀጣይነት መሰረት ነው" ያሉት ደግሞ የዳንግላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የህልውና ዘመቻ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ በለው ዘውዴ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም