የ"ወደ ሀገር ቤት እንግባ" ጥሪ መተላለፉ ለገጽታ ግንባታ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል

51

እንጅባራ፣ ህዳር 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማስተላለፋቸው የአገርን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አየነው ፋንታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ጥሪ የሀገርን ግንባታና ዕድገት ለማፋጠን አስተዋጾው የጎላ ነው።

አሁን ላይ  የኢትዮጵያ ታሪካዊ  የውጭ ጠላቶች በተላላኪያቸው አሸባሪው ህወሃት አማካኝነት ጦርነት በመክፈት ንጹሃን ዜጎችን ለመከራና ስቃይ የዳረጉበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሳል መሪነት በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ባጭር ጊዜ ውስጥ አኩሪ ድል ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል ።

"የተመዘገበው ድል ኢትዮጵያ ለዘመናት አስጠብቃው የኖረችው ነጻነት ዛሬም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስቻላል" ሲሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸው የአገርን ገጽታ ለመገንባትና የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጫናም ለመቋቋም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የደረሰውን መጠነ ሰፊ የሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት በሚካሄደው መልሶ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ሃብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ተጠቅመው በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት እድገትን በማፋጠንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አዲስ እድል ይከፍታል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ  አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን የሀገር ገጽታን ለማበላሸት  የሚያደርጉትን ድርጊት ለማክሸፍ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና የሥነ-ተግባቦት መምህር አቶ ታደለ አምበሉ ናቸው።

በአገራችን ያለውን የሰላም ሁኔታ ከማስገንዘብ ባሻገር አንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀንና ተቋማት ተጠምደውበት የከረሙበት የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት የተዛባ መሆኑን ለአለም ለማስገንዘብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ታደለ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ስላለው ዕውነታና ፍላጎት ለዓለም የሚያስተጋቡ፣ የሚሞግቱና ገጽታዋን የሚገነቡ ሚሊዮን የዲፕሎማሲ አጋሮችን ማሰለፍ ያስችላል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆችም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በሰላምና የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ምሁራኑ ጠይቀዋል።   

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም