ለግጦሽ እጥረት ለተጋለጡ እንስሳት 16 የጭነት ተሽከርካሪ የእንስሳት መኖ ድጋፍ ተደረገ

93

ጂንካ ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) የጋሞ ዞንና የአማሮ ልዩ ወረዳ አስተዳደሮች በዳሰነች ወረዳ በግጦሽ እጥረት ለተጎዱ እንስሳት የመኖ ሣር ድጋፍ አደረጉ።
አስተዳደሮቹ 900 ሺህ ብር ግምት ያለው የመኖ ሣር ቦታው ድረስ በማጓጓዝ ዛሬ አስረክበዋል።

በስፋራው ተገኝተው ድጋፍ ያደረጉት የአማሮ ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ ወረዳቸው የክልሉን ጥሪ ተቀብሎ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የዳሰነች ወረዳ ቀደም ሲል በአማሮ ወረዳ ተከስቶ በነበረው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በግንባር ቀደምትነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

"እኛም ተሞክሯቸውን በመውሰድ ዛሬ በተራችን ልንደርስላቸው በመወሰን 400 ሺህ ብር ግምት ያለው የሳር ድጋፍ አድርገናል" ብለዋል ።

የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲቆ ቲላንቴ በበኩላቸው በዳሰነች ወረዳ በተከሰተው ድርቅ በርካታ ብቶች መሞታቸውን ገልጸዋል።

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በዞኑ ህዝብና አስተዳደር ቅንጅት ግምቱ 500 ሺህ ብር የሆነ የመኖ ሣር ዛሬ ለዳሰነች ወረዳ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደር ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ቀብራራው ተክሌ በበኩላቸው እንስሳትን ከጉዳት ለመታደግ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  

በአካባቢው ከተከሰተው ድርቅ ስፋት አንፃር ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ መደበኛ የመፋሰሻ አቅጣጫውን ለቆ በመውጣቱ በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ከ45ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች ተፈናቅለዋል።

አካባቢውን ያጥለቀለቀው የጎርፍ ውሀ 200ሺህ የሚጠጉ የቤት እንስሳትን ለመኖ እጥረት እንዲጋለጡ ማድረጉን በወቅቱ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም