በግንባር የተሸነፈው አሸባሪ ሃይል በጥፋት መልእክተኞቹ ችግር እንዳያደርስ የአካባቢያችን ጸጥታ እየጠበቅን ነው

85

 አዲስ አበባ  ህዳር 30/2014 /ኢዜአ/ ግንባር የተሸነፈው አሸባሪ ሃይል በጥፋት መልእክተኞቹ ጥፋት እንዳያደርስ የአካባቢያቸውን ጸጥታ እየጠበቁ መሆናቸውን ወጣቶች ተናገሩ።

በግንባር በተገኙ ድሎች ሳንዘናጋ ለአካባቢያችን ሰላምና ጸጥታ የምናደርገው ጥበቃም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ አባባ ከተማ ምሽቱን ተዘዋውሮ በተመለከተባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ጥበቃ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጧል።

የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና የጸጥታ ሃይሎች የመዲናዋን ሰላም ለማስጠበቅ በትብብርና በመነጋገር እየሰሩ ይገኛሉ።

በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በግንባር እያስመዘገቡ ያሉት ድል ሁላችንንም አኩርቶናል ብለዋል።

በግንባር የተሸነፈው አሸባሪ ሃይል በጥፋት መልእክተኞቹ አማካኝነት ችግር ሊፈጥር ስለሚችል በየአካባቢያችን የጸጥታ ጥበቃውን አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገልጸውልናል።

በሰራዊታችን በተገኙ ድሎች ሳንዘናጋ ለአካባቢያችን ሰላምና ጸጥታ የምናደርገው ጥበቃ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት አካባቢ በጥቃ ስራ ላይ ያገኘነው ወጣት ጸጋዬ አፍሬም፤ “እኔም ለሀገሬ ዘብ ነኝ” በሚል መርህ የአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይናገራል።

በክፍለ ከተማው በፀጥታ ጥበቃ ላይ ያገኘነው ሌላኛው ወጣት ደመላሽ አበባየሁ፤ ለአካባቢያችን ሰላምና ጥበቃ ስራ ሁላችንም በባለቤትነት እየሰራን ነው ብሏል።

ማህብረሰቡም ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ለጸጥታ ሃይሎች ተባባሪ ሆኖ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

አሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈጠሩትን የጥፋት ጥምረት እኛም በጋራ ሆነን በማምከን ለህልውናዋ ቆመናል ብለዋል ወጣቶቹ።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ምሽቱን በጸጥታ ጥበቃ ላይ ያገኘነው ቴዎድሮስ ወርቁ፤ በከተማችን ከጫፍ ጫፍ የተጠናከረ ጥበቃ እየተካሄ ነው ይላል።

በክፍለ ከተማው በጸጥታ ጥበቃ ስራ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሀሊመት ጀማል፤ ለከተማችን ጸጥታ ሁላችንም እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"እኛ እናቶች እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢያችንን በመጠበቅ ለወጣቶችና ፖሊሶች በማስረከብ የማይቋረጥ የጸጥታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም