በዓባያ ሀይቅ ላይ እንቦጭ አረም እየተስፋፋ መሆኑ ተገለፀ

61
አርባምንጭ ነሀሴ 18/2010 በዓባያ ሀይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣው  እንቦጭ አረም ለብዝሃ ህይወት መጥፋትና ለአካባቢው ማህበረሰብ  ስጋት መፍጠሩ ተገለፀ፡፡ በአገሪቱ ከጣና ሃይቅ ቀጥሎ በስፋቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና 1 ሺህ 160 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ዓባያ ሀይቅ በእንቦጭ አረም ከተወረረ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህም በሐይቁ ውስጥ በሚኖሩ ብዝሃ ህይወትና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ስጋት መደቀኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በምዕራብ ዓባያ አልጌ ቀበሌ የሰላም ዓሣ አስጋሪዎች ማህበር ፀሐፊ ወጣት ሞገስ መኮንን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት አረሙ በፍጥነት የሚራባ በመሆኑ የውሃውን አካል በስፋት እየሸፈነ ይገኛል፡፡ ይህም በሚያሰግሩት ዓሣ መጠን ላይ ተጽእኖ ከማሳደሩ በላይ በሐይቁ የሚተዳደሩ ማህበረሰብ ክፍሎችን ስጋት ውስጥ የጣለ በመሆኑ የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ መጤ አረሙ እርስ በርስ በመጠላለፍ አንድም ሣር እንዳይበቅል ተጽእኖ በመፍጠሩ በሐይቁ አቅራቢያ የእንስሳት መኖ ሣር እየጠፉ ነው ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጫኖ ሚሌ ቀበሌ አርሶ አደር ባበና ዛዋ ናቸው፡፡ ባለፈው ጥር ወር ላይ አረሙ እንዳይስፋፋ በህዝብ ተሳትፎ የማስወገድ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም  ተከታታይነት ያለው ጥረት ባለመደረጉ አረሙ እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን አከባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ኩማ በበኩላቸው እንቦጭ አረም 1 ሺህ 705 ሄክታር የሚሆን የሐይቁን አካል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡ ከአራት ወር በፊት ከደቡብ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት እንዲሁም ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ባለስልጣን ጋር በመሆን በ15 ሺህ 620 ህዝብ ተሳትፎ 36 ሄክታር እንቦጭ አረም ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ እንቦጭ  የአከባቢውን ስነ-ምህዳር የሚያዛባ፣ በውሃ ውስጥ የኦክስጂን ዝውውርን በመግታት በውስጡ የሚገኙ ብዝሃ ህይወትን እንደሚያጠፋ አስረድተዋል፡፡ አረሙን በዝናብ ወቅት ለማስወገድ የማይመች ከመሆኑም በላይ በሐይቁ ውስጥ አዞና ጉማሬን ጨምሮ በርካታ የሚተናኮሉ እንስሳት መኖር አረሙን ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ ዘመናዊ ማሽን በመኮናተርና ህብረተሰቡን በማስተባበር አረሙን ለማስወገድ ከክልሉ አከባቢ ጥበቃና ደን ልማት ቢሮ ጋር ለመስራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም