ኀብረተሰቡ በህልውና ዘመቻው እየተመዘገበ ባለው ድል ሳይዘናጋ አሁንም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አለበት

59

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) ኀብረተሰቡ በህልውና ዘመቻው እየተመዘገበ ባለው ድል ሳይዘናጋ አሁንም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ ፡፡
 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ  ፋንታ እንዳሉት የከተማዋ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እያከናውነ ባለው ስራ የመዲናዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የአዲስ አበባን ሰላም ለማወክ የሚሹ የአሸባሪ ኃይሎችን ፍላጎት ማክሸፍ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ኀብረተሰቡ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ኮማንደር ፋሲካው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ፓሊስ ከኀብረተሰቡ ባገኘው ጥቆማና ባደረገው ተከታታይ ፍተሻ ለጥፋት ማስፈጸሚያ ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ንብረቶችን መያዙንም አስታውሰዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉ የጦር መሳሪያዎች መካከል በግለሰብ እጅ ሊኖሩ የማይገባቸው ቦንቦች እና የጦር ሜዳ መነፅሮች እንደሚገኙበትም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ኀብረተሰቡ በህልወና ዘመቻው እየተመዘገበ ባለው ድል ሳይዘናጋ አካባቢውን ነቅቶ የመጠበቁን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኀብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት እንደከዚህ ቀደሙ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ገልጸው፤ ፖሊስ ለሚደርሱት ጥቆማዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ኀብረተሰቡ በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥመው በነጻ የስልክ መስመር  991 በመደወል አሊያም በአካባቢያቸው ለሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አባላት ጥቆማ መስጠት እንደሚችል አስታውቀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም