ኀብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንቅ የሆነውን ሙስናን በመታገል መድገም ይጠበቅበታል

78

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29/2014(ኢዜአ) ኀብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንቅ የሆነውን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመታገል መድገም እንደሚጠበቅበት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ- ሙስና ቀን በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አክብረዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል አህመድ ሃምዛ በዚህን ወቅት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ዓላማን ሰንቆ በህዝብና መንግስት ሃብት ላይ ውድመት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በፈታኝ ወቅት በሙስናና በሌሎች ብልሹ ተግባራት ተሳታፊ በመሆን ለአገሪቱ ተጨማሪ ችግር ለመሆን የሚሰሩ አካላትን አጥብቆ መዋጋት እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ በአንድነት መቆማቸውን አንስተው፤ በተመሳሳይ በሙስናና ብልሹ አሰራር ኢኮኖሚውን ለመጉዳት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ከድህነት ለማውጣት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

በተለያዩ መስኮች አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ በመጠቀም እና ለሚፈለገው ዓላማ ብቻ በማዋል ለአገሪቱ ለውጥ መትጋት እንደሚገባም አንስተዋል።

ሁሉም በየተሰማራበት መስክ አገርን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል የዜግነት ድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

ሌሎች የሠራዊቱ አባላት በበኩላቸው፤ በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ እና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ከስር ጀምሮ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ማፍራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ መስራት እንደሚኖርበት ገልጸው፤ በተለይ በየደረጃው ያሉ ህዝብን የሚያገለግሉ አመራሮች ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ሁሉም የድርሻው መወጣት ከቻለ ሙስናን ማስቀረት እንደሚቻል ሻምበል ሙሉጌታ ካሳ ይገልፃሉ፡፡

መቶ አለቃ ኡፋይሳ ኡቃ በበኩላቸው ሙስና ብር መቀበል ብቻ ሳይሆን ከአስተሳሰብ ይጀምራል አስተሳሰቡን ለማስወገድ ህብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ስራዎች ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡

"ሙስና ሌብነት ነው በመሆኑ ከቤት ውስጥ ይጀምራል ካሉ በኋላ አመራራሩ ከሙስና የፀዳ ሲሆን ከስሩ ያለው ሰራተኛም ያንን ይከተላል "ብለዋል አስር አለቃ በያን ጅብሪል፡፡

የዘንድሮ የፀረ-ሙስና ቀን "በስነ-ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም