ከደብረ ብርሃን ከሚሴ ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ነገ ይጠናቀቃል

92

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) ከደብረ ብርሃን እስከ ከሚሴ ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና እስከ ነገ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል አሸባሪው ህወሓት መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ውድመትና ዝርፊያ መፈጸሙን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የደረሰው ጥፋት ከቦታ ቦታ የሚለያይ በመሆኑ የጉዳቱ መጠን እየተጠና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በጋሸና፣ በደብረ ብርሃን እና በሚሌ ኮምቦልቻ መስመሮች የሽብር ቡድኑ ወራሪ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት መፈፀሙን አረጋግጠዋል።

በሃይል ማስተላለፊያና ለዚሁ አገልግሎት በተገጠሙ የሕዝብ ንብረቶች ላይ ከደረሰው ውድመት በተጨማሪ አገልግሎት ባልጀመሩ የሃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች ላይ ዝርፊያ መፈፀሙንም ተናግረዋል።

በተለይም ባህር ዳር፣ ደሴ እና ኮምቦልቻን የሚያገናኘው አዲሱ የኤሌክትሪክ ሃይል ዝርጋታ ፕሮጀክት ሃብት የሆኑና በመቄትና በጋሸና ተከማችተው የነበሩ በርካታ ንብረቶች መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ጋሸና እና ደብረ ብርሃን መስመር እንዲሁም በአፋር ክልል ከሚሌ ኮምቦልቻ በሚወስደው መስመር ተቋሙ የጥገና ቡድን አሰማርቶ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በሶስቱም አቅጣጫዎች የተጀመረው ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ ከደብረ ብርሃን እስከ ከሚሴ ያለው ከፍተኛ ሃይል ተሸካሚ መስመር ጥገና ነገ ይጠናቀቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በእስካሁን እንቅስቃሴም ቀላል ጉዳት የደረሰባቸውና በበርካታ አካባቢዎች የሚገኙ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው የኤሌክትሪክ ሃይል መስት መጀመራቸውን አረጋግጠዋል።

ሸዋሮቢት፣ ደብረ ሲና፣ ጣርማ በር፣ ዬለን እና ሞላሌን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ካገኙት ከተሞች መካከል ጠቅሰዋል።

ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያለውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና እንደተጠናቀቀ በአገልግሎት በኩል ያለውን ቀሪ ስራ በቅንጅት በመከወን ኅብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ኃይል እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም