የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደም ሀሰተኛ ዘገባን መመከት አለባቸው

130

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማከል አድርገው፣ አገር ላይ የተከፈተውን ሀሰተኛ ዘገባ መመከት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በአሻባሪው ሕወሓት አማካኝነት በተከፈተባት የውክልና ጦርነት መልከ ብዙ ፈተናዎችን እያስተናገደች ትኛለች።

ከፈተናዎቹ መካከል ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሓን ድረስ በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጩ ያሉት ሀሰተኛ መረጃ አንዱ ነው።

የሀሰተኛ መረጃ ስርጭቱ በማሕበራዊ ሚዲያው የታገዘ መሆኑ ደግሞ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ከፍተኛ መሆኑን አመላካች ነው።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመመከት የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል አድረገው መስራት አለባቸው ይላሉ ሙያተኞቹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባልደረቦች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ጎልቶ እየታየ መሆኑን አንስተዋል።

የባለስልጣኑ የንግድ ብሮድካስት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሌሊሳ ተረፈ፣ የራሳቸውን አጀንዳ ማራመድ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ሆን ብለው ሀሰተኛ ዘገባዎችን በመፈብረክ ያሰራጫሉ ብለዋል።

ይህ ጉዳይ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ጎልቶ እንደሚታይ እና ዋና ዓላማውም ኢትዮጵያን ማዳከም እንደሆነ ይናገራሉ።

ሀሰተኛ መረጃዎች በበዙበት በዚህ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የኢትዮጵያን እውነታ ማሳወቅና ሀሰተኛ መረጃን በማጋለጥ ተግተው መስራት አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ጋዜጠኞች ለሙያው ሰነ-ምግባር መርሆዎች ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።

በዋናነት ግን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማዕከል አድርገው የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

በባለስልጣኑ የዋና ዳሬክተሩ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ደጄኔ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሓን ሙያተኞች ስራቸውን ሲያከናውኑ ሕጎችን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው ይላሉ።

አቶ ታምራት እንደሚሉት ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ ከመረጃ ነጻነት ጋር ተያይዘው የወጡ ሕጎች ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን ይከለክላሉ።

ከሁሉም በላይ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ አውቆና አክብሮ መስራት የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሲሆን ሙያተኞቹ የራሳቸውን ተጋላጭነት ቀንሰው፣ በአገር ላይ የተከፈተውን ዘመቻም መመከት ይችላሉ ነው ያሉት።

አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሆን ብለው በሚመሰል መልኩ በየቀኑ በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጯቸው ይሉ የተዛቡና ሀሰተኛ ዘገባዎችን በተደራጀ መንገድ የማጋለጥና የመመከት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም