አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ለበጋ መስኖ ስራዎች ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው

113

ጎባ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ ዞን የጊኒር እና ዳዌ ቃቸን ወረዳዎች አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በዝናብ እጥረት ሳቢያ ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ለማካካስ ለመስኖ ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
በክልሉ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በሁለት ዙር ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል።

በጊኒር ወረዳ በልማቱ ከተሳፉ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብዱሰላም ሀሰን እንዳሉት ያለፈው የመኽር ዝናብ ስርጭት ጊዜና በሚፈለገው መጠን ባለመዝናቡ በሰብል ምርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡

በመሆኑም በዚህ ሳቢያ ሊቀንስ የሚችለውን ምርት የአካባቢያቸው የውኃ ሀብት ተጠቅመው ለማካካስ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር አብዱረህማን በከር መንግሥት የውሃ መሳቢያ ሞተርና የምርጥ ዘር ድጋፍ ስላደረገላቸው በልማቱ ከመደበኛው የእርሻ ስራ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴ በመስኖ ማልማት ጀምረዋል፡፡

በመስኖ ልማቱ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ገበያ ተኮር  የሆኑ የፓስታና መካሮኒ ስንዴ በማምረት ገቢ ለማግኘት አልመው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዳዌ ቃቸን ወረዳ በመስኖ ልማቱ የተሳተፉት ሼህ ሀሰን አህመድ እንዳሉት የአካባቢው ማህበረሰብ ከእንስሳት እርባታ ውጭ በእርሻ ሥራ የመሳተፍ ልምድ አልነበራቸውም፡፡

ከመንግሥት ባገኙት የውሃ መሳቢያ ሞተርና ምርጥ ዘር ድጋፍ ባለፈው የበጋ ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን በመስኖ አልምተው ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራትም አምናው ያገኙትን ተሞክሮ ቀምረው የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአቅራቢያቸው ያለጥቅም ሲፈስ የነበረውን የወንዝ ውሃ በሞተር ስበው የስንዴ ሰብል፣ ቲማቲምና ሌሎች የጓሮ አትክልት እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ከድር ሱልጣን ናቸው።

በዘንድሮ የምርት ወቅትም ሌሎች አርሶ አደሮች ውጤታማ የሆኑበትን የተሻሻለ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ተጠቅመው ከአምና የተሻለ ምርትና ገቢ እንደሚጠብቁም ተናግረዋል ።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሹክሪ ጠሃ እንዳሉት አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች የአካባቢያቸውን የውኃ ሀብት ተጠቅመው ስንዴ በመስኖ እንዲያለሙ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በተለይም ከውጭ ሀገር የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ ለመተግበር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ ስምንት ወረዳዎች በአንደኛ ዙር ከ6 ሺህ 400 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በመጀመሪያው ዙር የመስኖ በተደረገው እንቅስቃሴ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል።

የልማቱ ተሳታፊዎች ውጤታማት እንዲሆኑ ከ200 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞቶሮች በረዥም ጊዜ ክፍያ  ብድር ገዝተው እንዲጠቀሙ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንዳሉት ከውጭ ሀገር የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ለመተካት ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ኃላፊው እንዳሉት በመጀመሪያው ዙር በተደረገው ጥራት በሕቅድ ከተያዘው መሬት ውስጥ  ግማሽ ያህሉ በመስኖ የማልማት የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህም ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በክልሉ ደረጃ በዘንድሮው የመኽር ወቅት ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ198 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ላምረት መታቀዱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም