የወደሙ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ ነው -አቶ ስዩም መኮንን

132

ባህር ዳር ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወደሙ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

በክልሉ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን የመሰረተ ልማት ውድመት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማስጠናት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በውይይቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።

የአሸባሪው ወራሪ ሀይል የግልና የመንግስት ንብረት ከሆኑት ባለፈ የህዝብ መገልገያ በሆኑ የትምህርት፣ የጤናና መሰል ተቋማት ላይ እንደሁም  የኢንቨስትመንት መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን አመልክተዋል።

ወረራ በተፈፀመባቸው አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች በሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ሃይል፤ ሚሊሻና ፋኖ  ተጋድሎ ነፃ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ከወራሪው ሃይል ነፃ በወጡ አካባቢዎች መደበኛ የሆኑ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመርና መልሶ ለማቋቋም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስት በወደሙ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት በሳይንሳዊ መንገድ በማስጠናት ወደ ነበሩበት ለመመለስ ኮሚቴ ማቋቋሙን ተናግረዋል።

"ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማጥናት የዩኒቨርሲቲ ምሁራኖች ሚና የጎላ ነው" ሲሉም አመልክተዋል ።

የሚከናወነው ጥናት የክልሉን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በአሸባሪው ቡድን አስፈላጊውን ፍርድ እንዲያገኝ ጉልህ ድርሻ እንዳለው አቶ ስዩም አስታውቀዋል።

ዛሬ በተጀመረው የውይይት መድረክ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ባላድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የጥናት እቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ ከመርሀ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም