የኢትዮጵያ አንድነት በህብረ-ብሔራዊነትና ህዝቦች እኩልነት ደምቆ ይኖራል

124

ህዳር 29/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ አንድነት በህብረ-ብሔራዊነትና ህዝቦች እኩልነት ደምቆ ይኖራል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ ገለጹ፡፡
16ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባዓል "ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ከከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ እንደተናገሩት፤ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ትስስር በሚያጎለብት መልኩ ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት በህብረ-ብሔራዊነትና በህዝቦች እኩልነት ደምቆ ይኖራል ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ሁሉም ዜጋ  አንድነቷ የተከበርና ጠንካራ አገር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የበዓሉ መከበር የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ጠብቆ ለማቆየት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ሲከበር ከልዩነት ይልቅ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም