የአዲስ አበባ ሆቴሎች "የአገር ልጅ" የሚል 'ፓኬጅ' ሰይመው ለገና በዓል ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል

56

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሆቴሎች "የአገር ልጅ" የሚል 'ፓኬጅ' ሰይመው ለገና በዓል ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ባለፈው ሳምንት ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች የገናን በዓልን አገራቸው መጥተው እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በቅርቡም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ሆቴሎች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሃ በቀለ፣ ጥሪውን አስመልክቶ የኮከብ ደረጃ ያላቸውን ሆቴሎችን ጨምሮ በማኅበሩ ሥር ያሉ ከ175 በላይ ሆቴሎች ጋር ምክክር በማድረግ "የአገር ልጆች አርሂቡ" በማለት በመልካም መስተንግዶ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ሆቴሎቹ "የአገር ልጅ" የሚል 'ፓኬጅ' ሰይመው ዳያስፖራዎችንና የኢትዮጵያን ወዳጆች ተቀብለው ለማስተናገድ "ሽርጉድ" እያሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ'ፓኬጅ' በተጨማሪ እንግዶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

የጥራት ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በማህበሩ በኩል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች እንግዶችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ባህል የመቀበል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ አምሃ ጠይቀዋል።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ለመቀበል የሚያስችል ግብረ ሃይል የሚቋቋም መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም