ኢትዮጵያ ክብር እና ሉዓላዊነቷን እያስከበረችበት ያለው መንገድ ለአፍሪካዊያን አርአያ የሚሆን ነው

55

ህዳር 29/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የሕልውና አደጋ መክታ ክብርና ሉዓላዊነቷን እያስከበረችበት ያለው መንገድ ለሌሎች አፍሪካዊያን በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ዘመቻ ኢትዮጵያ በነፃነት ትግል እንቅስቃሴ ወቅት የነበራትን የመሪነት ሚና ዳግም ያረጋገጠ  መሆኑም ተገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የሕልውና ዘመቻ የምዕራባዊያን ጫና ላለባቸው አገራት ጭምር እንደ ዓርአያ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ነው የተናገሩት።

አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት ከወጡ ማግስት ጀምሮ በተለያየ መንገድ የሚደረገው ጫና አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን አብራርተዋል።

ምሁራኑ እንደሚሉት የዚህ ዋነኛው መንስኤ ምዕራባዊያኑ በአፍሪካ አገራዊና አሕጉራዊ ራዕይ የሌለው አሻንጉሊት ስርዓት የማቋቋም ፍላጎት ነው።

አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያም ይህንኑ ፍላጎታቸውን ለመጫን ከለውጡ በኃላ እያደረጉት ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጫና እየበረታ መምጣቱን አንስተዋል።

በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ያሬድ አስራት፤ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሉዓላዊነት ትግል በአፍሪካ አገራት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ዘመቻውን መቀላቀል በዚህ ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅና ምዕራባዊያንን ያስደነገጠ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ተገኝተው ኢትዮጵያዊያንን በማነሳሳት በርካታ ድሎች መመዝገባቸው ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ መካድ እንዳይችሉ አድርጓል ነው ያሉት።

ለዚህም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያናፍሱ የነበሩ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የመጡ ድሎችን እንዲዘግቡ መገደዳቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ላለው ጫና አንዱ መነሻ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላቸውን ጥቅም የሚያስከብርላቸው ተላላኪ ስርዓት ማቋቋም መሆኑን ነው ዶክተር ያሬድ የገለጹት።

ጫናው የኢትዮጵያን እና የሕዝቧን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ አገራዊ ራዕይ የሌለው ስርዓት የመመስረት ፍላጎት መሆኑንም ጠቁመዋል።

አፍሪካዊያን ጫናው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የተቃጣ ሳይሆን በእነርሱም ላይ የሚደርስ መሆኑን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የጠቀሱት ዶክተር ያሬድ "ይህን ተፅዕኖ ለመመከት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፈለግ መከተል ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር ሃይሌ ሙላቱም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።

የኢትዮጵያ ትግል በአርዓያነት የሚጠቀስ፣ በእሷ መሪነት የተነቃቃው የውጭ ጫናን የመመከት የተቃውሞ ንቅናቄም ለሌሎችም አገራት ነፃነት ትልቅ አርዓያ ይሆናል በሚለው።

የአፍሪካን ነፃነት ለማረጋገጥ በሚደረግ የምሁራን ንቅናቄ ሲሳተፉ መቆየታቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ገብሬ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሕልውና ትግል አፍሪካዊያን ሊደግፉት ይገባል ባይ ናቸው።

ለዚህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚደግፉ አገራት ጋር ያለውን ትስስር ማጎልበትና ውስጣዊ አቅምን አቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዶክተር ሃይሌ ሙላቱም እንዲሁ "አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ እየተፈፀመ ያለው የምዕራባዊያን ጫና በመላው አፍሪካ ላይ የተቃጣ መሆኑን በመረዳት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

የእስካሁኑ የአፍሪካዊያን ትብብር ያልተቀናጀ በመሆኑ ዋጋ ማስከፈሉን የገለፁት ዶክተር ሃይሌ "የአፍሪካን ነፃነት ማረጋገጥ የሚቻለው የአፍሪካ ኅብረት በሚወስዳቸው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች ነው" ይላሉ።

ለዚህም በአንድ ልብ እንደ አንድ አገር መንቀሳቀስና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የነፃነት ትግል መቀላቀል፤ ብሎም በተግባር የተደገፈ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም