ቢሮው ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

76

አዲስ አበባ ህዳር 29/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በመዲናዋ ከሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ይስራ እድል ፈጠራን በተቀናጀ መልኩ እውን በማድረግ በርካታ ዜጎችን የእድሉ ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑ ተመልክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እና የቢሮው ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ከተቋማቱ ተወካዮችና ኃላፊዎች ጋር ስምምነቱ ተግባራዊ በሚደረግበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።  

በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከማን ምን ይጠበቃል? ቅንጅቱ እንዴት ይጠናከር? የሚሉ ጉዳዮች የውይይቱ ዋነኛ ነጥቦች ሲሆኑ ከውይይቱ በኋላ የሥራ ፈጠራ ሥራዎችን በትብብር ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት አድርገዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው ባለፉት አምስት ወራት በሥራ ፈጠራ ላይ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰው በቀጣይ የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

መልካም እድሎችን ሁሉ ተቋማት ለሥራ እድል ፈጠራ መጠቀም አለባቸው ያሉት አቶ ጃንጥራር በተደረገው ስምምነት መሰረት እንዲተገብሩም አሳስበዋል።

የሥራ እድል ለመፍጠር ምን ምቹ ሁኔታ አለኝ? ለስንት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር እችላለሁ? የሚለውን ተቋማት ማጤን እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።  

የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚከታተል የቴክኒክ ኮሚቴ መደራጀቱን ጠቁመው፤ አፈጻጸሙን በየጊዜው እየተከታተለ የሚገመግም አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም ጠቁመዋል።  

አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ራሱን የቻለ የሥራ እድል ፈጠራ እቅድ እንዲኖራቸው ይጠበቃል ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በፈጠሩት የሥራ እድል ልክ የሚገመገሙ ይሆናል ብለዋል።

በአምራቹ ዘርፍ፣ በንግድና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የኢንዱስትሪና ግንባታ ዘርፍን ጨምሮ ለዜጎች የሥራ እድል የመፍጠሩ እንቅስቃሴ ይጠናከራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም