አናሶራ ወረዳ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

93

ነገሌ፤ ህዳር 29/2014(ኢዜአ)  በጉጂ ዞን የአናሶራ ወረዳ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ፡፡
የወረዳው የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቲሴ ጃርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት የወረዳው ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች በቅርቡ የተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ለ4ኛ ጊዜ 51 ሰንጋዎችን ለመከላከያ ሰራዊት በድጋፍ  አበርክተዋል።  

የወረዳው የመንግስት ሰራተኞችም የወር ደመወዛቸውን በመስጠት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ህዝቡ በስንቅ ዝግጅትና በደም ልገሳ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው አጠቃላይ ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብና በአይነት 10 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል ።

በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ላሉ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

ህዝቡ አካባቢውን ከሽብር ጥቃት ነቅቶ ከመጠበቅ ጎን ለጎን ልጆቹ መከላከያ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ መርቆ እየላከ መሆኑን ሀላፊው አስታውቀዋል።

በወረዳው ባለሀብት የሆኑ አቶ ሸዋንግዛው ቦጋለ  በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ለህልውና ዘመቻው በሁለት ዙር በጥሬ ገንዘብ ካደረጉት 66 ሺህ ብር ድጋፍ በተጨማሪ አሁን ላይ ለ3ኛ ጊዜ በ45 ሺህ ብር ሰንጋ ገዝተው ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በሶስት ዙር በጥሬ ገንዘብ 27 ሺህ ብር፤ አሁን ደግሞ 40 ሺህ ብር ዋጋ ያለው ሰንጋ ማበርከታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ባለሀብት አቶ ሸርዴ ባሊ ናቸው።

የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር የህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ላለው መከላከያ ሰራዊት ወደ ፊትም ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለሀብቶቹ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም