የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ማጣሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ከሩዋንዳ ጋር ያደርጋል

117
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 በታንዛንያ እየተካሄደ ባለው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ክፍለ አህጉሩን(ሴካፋን) ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። የምድብ ጨዋታዎችን መጠናቀቅ ተከትሎ ዛሬ በታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከቀኑ 8 ሰዓት ከሩዋንዳ ጋር ይጫወታል። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ ሁለት ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ በ12 ነጥብና በ11 የግብ ክፍያ ምድቡን በመሪነት አጠናቆ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፏል። ብሔራዊ ቡድኑ በታንዛንያ እያሳየ ባለው ብቃት የእግር ኳስ አፍቃሪው አድናቆት እየቸረው ሲሆን በአራቱ ጨዋታዎች 14 ግብ አስቆጥሮ ሶስት ግብ አስተናግዷል። ከትናንት በስቲያ ብሔራዊ ቡድኑ ኬንያን 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ሶስት ጎል በማስቆጠር ሀትሪክ የሰራው በየነ ባንጃና በአራቱም ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረው ምንተስኖት እንድርያስ በውድድሩ ላይ ጥሩ ብቃት እያሳዩ ይገኛሉ። የሩዋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ አዘጋጇን ታንዛንያን ተከትሎ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉ የሚታወስ ነው። አዘጋጇ ታንዛንያና ኡጋንዳ  ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ሩዋንዳን አሸንፎ በፍጻሜው ጨዋታ ከአዘጋጇ ታንዛንያ ጋር የሚገናኝ ከሆነ በ2011 ዓ.ም በታንዛንያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ክፍለ አህጉሩን(ሴካፋን) ወክሎ መሳተፉን ያረጋግጣል። ታንዛንያ የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር አዘጋጅ በመሆን በውድድሩ ላይ የምትሳተፍ በመሆኑ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በታንዛንያ ቢሸነፍም ሴካፋ ዞንን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ውድድር ላይ ይሳተፋል ማለት ነው። የፍጻሜና የደረጃ ጨዋታዎች በታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም ከነገ በስቲያ ይደረጋሉ። የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም