እንዳሻው አላዩ በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ

69
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 እንዳሻው አላዩ በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። በሃንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት እየተካሄደ ያለው 6ኛው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ከነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የክብደት ዘርፎች በመካሄድ ላይ ይገኛል። በ49 ኪሎ ግራም የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው እንዳሻው አላዩ ኢኳዶራዊውን ቦክሰኛ ጆናታን ሜርቻንን በነጥብ በማሸነፍ ወደ 16 ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው። የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ትናንት ማምሻውን ከአርሜንያዊው ሴይራን ዬጊክያን ጋር አድርጎ በነጥብ በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ መግባቱን  የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ቀጣይ ጨዋታውን ነገ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። ከትናንት በስቲያ በ48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክላ የተጫወተችው ሀና ደረጀ በአሜሪካዊቷ ሳንድራ ቶቫር ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ መሆኗን አስታውሰዋል። የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም