የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ በተደራጀ አግባብ እየተሰራ ነው

56

ደብረ ታቦር ፤ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ጎንደር ዞን የደብረ ታቦር ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በተደራጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።
አሸባሪው ህወሓት አስርጎ ያስገባቸው ብዛት ያላቸው የጥፋት ተላላኪዎች  በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመላክቷል።

የኮሚቴው ሰብሰቢና የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ባሻ እንግዳው፤ የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተላላኪዎች ተመሳስለውና ሰርገው በመግባት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ እንደተደረሰባቸው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ይህም አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች አንዳንድ አካባቢው ወረራ በመፈጸም  ጉዳት ያደረሰው ተዋግቶ በማሸነፍ ሳይሆን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን በማሸበር እንደሆነ አመልክተዋል።

ከተማዋን ለመሰለልና ጉዳት ለማድረስ ተመሳስለው ሰርገው የገቡ ብዛት ያላቸው የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።

እነዚህ ተላላኪዎች ከሰሜን ወሎ ዞን ለግብይትና ከባንክ ብር ለማውጣት ወደ ከተማ ከመጡ ግለሰቦች ጋር ተመሳስለው ሲገቡ በጸጥታ አባላት፣ በህብረተሰቡ ጥቆማና  ፍተሻ መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለሰራዊቱ ደጀን ከመሆን ባለፈ በተለያየ አደረጃጀት አካባቢውን ሌት ተቀን እየጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፤ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥሙት ለፀጥታ መዋቅሩ የሚሰጠውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ወጣት ፍቃዱ ነጋ በበኩሉ ''አካባቢያችንን በተለያየ አደረጃጀት ሌት ተቀን በፈረቃ እየጠበቅን የአሸባሪውን ህውሃት ሰርጎ ገቦች በመያዝ ለህግ እያቀረብን ነው'' ብሏል።

የአካባቢ ጥበቃና  ለሰራዊቱ የሚያደርጉትን ደጀን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጸው ወጣት ፍቃዱ፤  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ሰጭነት እየተገኘ ያለውን አመርቂ ድል ከዳር ለማድረስ እንደሚደግፍም ተናግሯል፡፡

 ''በግንባር እየተዋደቀ ላለው የጸጥታ መዋቅር ደጀን ከመሆን ባለፈ እኛም ግንባር ተሰልፈን ቡድኑን ፊት ለፊት ተፋልመን ነጻነታችን ለማስቀጠል ዝግጁ ነን'' ያለው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አንዳርጋቸው ወርቁ ነው።

በከተማዋ  ሰርጎ በመግባት የሀሰት ወሬ በመንዛትና ሽብር በመፍጠር የሚጠረጠሩ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ተከታትሎ የመቆጣጠሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል።

አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል በጋሸና ግንባር በደረሰበት ምት ያወደመውን አውድሞ  በመፈርጠጡ የተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ነጻ እየወጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም