ኢትዮጵያና ቬትናም የትብብር ስምምነቶች ተፈራረሙ

194
አዲስ አበባ ነሐሴ 17/2010 ኢትዮጵያና ቬትናም ሶስት የትብብር ስምምነቶች ተፈራረሙ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቬትናሙን ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግን በብሄራዊ ቤተ-መንግስት አነጋግረዋል። ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከፈረሟቸው ስምምነቶች መካከል በኢንቨስትመንት መስክ በትብብር መስራት ይገኝበታል። ሌሎቹ ስምምነቶች ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችና አገልግሎት ሰጪዎች ነፃ ቪዛ እንዲያገኙ እና የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች በፖለቲካ ላይ ምክክር ስለሚያደርጉባቸው ጉዳዮች  የሚያጠነጥኑ ናቸው። ፕሬዝዳንቶቹ በኢትዮጵያና ቬትናም መካከል ያለው የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና የማህበራዊ ትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይም መክረዋል። ከውይይቱ በኋላ ፕሬዝዳንቶቹ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የተሳካ ምክክር ማድረጋቸውን ገልፀዋል። አገራቱ በፖለቲካው መስክ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናግረዋል። በማምረቻው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥሩ ልምድ ያላቸው ቬትናማውያን መዋዕለ-ነዋያቸውን በኢትዮጵያ በማፍሰስ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ቃል ገብተዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ በግብርናና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች በትብብር ለመስራትም ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል። የቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን በበኩላቸው ወደምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ሁለቱ አገራት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ሰላም በማስከበር ሂደት የተሻለ ልምድና አስተዋፅኦ ያላት መሆኑን የተናገሩት የቬትናም ፕሬዝዳንት አገራቸው በሰላም ማስከበር ተግባራት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራት ትፈልጋለች ብለዋል። ኢትዮጵያና ቬትናም ነፃነታቸውን በማስጠበቅ ታሪክ ያላቸው አገራት በመሆናቸው ይህንን እሴት ይዘው በጋራ ትብብር መስራት ይገባቸዋል ሲሉም ፕሬዝዳንት ትራን ገልፀዋል። አገራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በአየር ትራንስፖርት፣ በተሽከርካሪ መገጣጠም፣ በቡናና ሻይ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደምትፈልግም ነው  የጠቀሱት። በማምረትና በግብርና ዘርፍ ቬትናም ያካበተችውን የረጅም ጊዜ ልምድ ለኢትዮጵያ እንደምታካፍል፤ አገራቸውም በተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመውሰድ እንደምትፈልግ ገልፀዋል። ቬትናምና ኢትዮጵያ የ42 አመታት ግንኙነት ቢኖራቸውም እስካሁን የተሳካ ትብብር እንዳልነበራቸው ነው የተገለፀው። በቀጣይ የተጀመረውን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ በሚኖራቸው ቀሪ ሁለት ቀናት ከህዝብ ተወካዮችና ከፌደሬሽን ምክር ቤቶች መሪዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም