በኢትዮጵያ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የመሬት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጠ

83
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በኢትዮጵያ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መሰጠቱን የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ። የዚህ ዓይነቱ የአርብቶ አደር የመሬት ማረጋገጫ ሲሰጥ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያ ነው ተብሏል። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩ ኤስ አይ ዲ)  ከግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች ላለፉት አምስት ዓመታት በመሬት አስተዳደር እና ክብካቤ ዙሪያ ሲያካሄድ የቆየውን ፕሮጀክት ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል። በዚሁ ፕሮጀክት ላይ የመከረ አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዷል። በፕሮጀክቱ ትግበራ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ውስጥ ለሚገኙ ሶስት የአርብቶ አደር አደረጃጀቶች የመሬት ይዞታ ባለቤትነት መረጋገጫ የምሰክር ወረቀት ተሰጥቷል። አርብቶ አደሮቹ በባህላዊ አደረጃጀት መሰረት በአባ ገዳ ስር በሚገኘው አባ ዴዳ (Abbaa Dheeda) አደረጃጃት አማካይነት የተመዘገቡ ናቸው። አባ ዴዳዎች በአካባቢው የግጦሽ መሬቶችን የሚያሰማሩ ባህላዊ አደረጃጀቶች ናቸው። በእነዚህ አደረጃጀቶች አማካኝነትም ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ምዝገባ ተካሄዶ ለባለይዞታዎቹ የመስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በዚህም ከ40 ሺህ በላይ የሆኑ አባራዎች ተጠቃሚ መሆናቸው በአውደ ጥናቱ ላይ ተገልጿል። የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳሉት የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ለማረጋገጥ በቦረና የተገኘውን ተሞክር ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማስፋት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በኢትዮጵያ ከ17 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ባለቤትነት መረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለመስጠት ምዝገባ እየተካሄደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የምስክር ወረቀቱን ወስደዋል። ሚኒስትር ዲኤታው እንዳሉት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱን የሚወስዱ አርሶ አደሮች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩ ኤስ አይ ዲ) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በመሬት ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ በመሬት አስተዳደር፣ የአቅም ግንባታ እና በአርብቶ አደር አካባቢ የመሬት አጠቃቀም ላይ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ደግሞ የድርጅቱ የግብርና ፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪና የመሬት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዘመነ ሐዲስ ናቸው። ድርጅቱ ፕሮጀከቱን ለማስፈፀም የፋይናንስና የቴክኒካል ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ሰጥቷል፤ 82 የመሬት ልማት ባለሙያዎችን በባህዳር ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ አድርጓል። ድርጅቱ ከግብርና እና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ፣ አፋር፣ አማራ፣ ደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደዚሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች የመሬት አስተዳደር ቢሮዎች ጋር በመሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል። የኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሜሬሳ ፊጤ እንዳሉት ድርጅቱ ከክልሉ ጋር በመሆን በሰራው ስራ አርብቶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት እንዲሰማውና መሬቱን እንዲንከባከብ ያደርጋል ብለዋል። ይህን በቦረና ዞን የታየውን ተሞክሮ ወደ ተቀሩት አራት የክልሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች ለማስፋት በቀጣይ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም