ከአሸባሪው ህወሃት ወረራ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተቋርጠው የነበሩ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል

118

ህዳር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአሸባሪው ህወሃት ወረራ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተቋርጠው የነበሩ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።

በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሯቸውን እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዶክተር አለሙ ስሜ እንዳሉት፤ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የመንግሥትና የግለሰብ ንብረት ዘርፏል፣ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል።

በዚህም የመብራት መስመሮች፣ የቴሌኮም ኔትወርክ፣ ውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ተቋርጠው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአሸባሪ ቡድኑን ወራሪ ኃይሎች ከመደምሰስ ጎን ለጎን የተቋረጡ የመሰረተ ልማት አውታሮች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል።

ከደብረሲና ጀምሮ ከሽብር ቡድኑ ወረራ ነፃ በወጡት ሸዋሮቢት፣ አጣየ እና ከሚሴ ከተሞች መሰረተ ልማቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮምቦልቻና ደሴ ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት የተጀመረ ሲሆን የውሃ፣ የቴሌኮምና የመብራት አገልግሎት ከቀናት በኋላ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን የጠቀሱት ዶክተር አለሙ፤ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ጨምሮ የመንግስት ሰራተኛውና ነጋዴው ወደ ስራው መመለስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት የተረፈው ሃብትና ንብረት በተገቢው ሁኔታ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አካባቢያቸውን ነቅተው እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም