የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የክልሉ ህዝብና መንግስት ሁለንተናዊ ደጀንነት ተጠናክሮ ይቀጥላል

61

ጋምቤላ፤ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ)፡ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የክልሉ ህዝብና መንግስት ሁለንተናዊ ደጀንነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የሰላምና ደህንነት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢ አህመድ ወደ ግንባር ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ አንጸባራቂ ድሎች እየተመዘገቡ ነው።

"የክልሉ ህዝብና መንግስት በህልውና ዘመቻው ደጀን ሆኖ በመታገልና በተለያዩ ተግባራት በመሳተፍ ግዴታችንን እየተወጣን ነው" ብለዋል።

የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የክልሉ ህዝብና መንግስት ሁለንተናዊ ደጀንነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በተለይም አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ ደጀንነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ክልሉ ጠረፋማና ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተሟላ መልኩ በመተግበር ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል የተጠናከረ የሰላምና ደህንነት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ የሆነውንና እራሱን የጋምቤላ ነፃነት አውጪ ግንባር (ጋነግ) በሚል የሚጠራው ቡድን በክልሉ ብጥብጥ ለመፍጠር ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማክሸፍ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

"ተላላኪ ቡድኑ የክልሉን ወጣቶች በገንዘብ አማሎ ለጥፋት ተልእኮ ለማሰለፍ ቢሞክርም አልተሳካለትም " ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ የሽብር ቡድኑን እኩይ ተልእኮ የተገነዘቡ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠታቸውን ጠቅሰዋል ።

የክልሉ መንግስት እጃቸውን ለሰጡ ወጣቶች አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ህይወት እዲመሩ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም