የእሑድ ገበያው ከዋጋ ማረጋጋት ባሻገር በእረፍት ቀን መከወኑ ተጠቃሚ አድርጎናል

71

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ)  በአዲስ አበባ የተጀመረው የእሁድ ገበያ ከዋጋ ማረጋጋትና ከአቅርቦት ስፋት ባሻገር በእረፍት ቀን መከናወኑ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ሸማቾች ገለጹ።

በመዲናዋ መካሄድ ከጀመረ አምስት ሣምንታት ባስቆጠረው የእሑድ ገበያ የአምራች ሸማች የቀጥታ ግብይት ሰንሰለት ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት መፈጸሙም ተገልጿል።

እየጨመረ የመጣውን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ ውድነት ለማቃለል የሸማች ኅብረት ስራ ማኅበራት በየሣምንቱ እሑድ በተመረጡ ቦታዎች ሸማቹን እያገበያዩ ይገኛሉ።

የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረቡ ዓላማ ኅብረተሰቡን ከሰው ሰራሽ የገበያ አሻጥሮችና ያልተገባ የዋጋ ንረት መከላከል ነው።

ኢዜአ በተዘዋወረባቸው የሰንበት ገበያዎች ያነጋገራቸው ሸማቾችም ግብይቱ የታለመለትን ዓላማ እያሳካ መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከአንድ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ገበያው በእረፍት ቀን መዋሉ እንዲሁም በቂ የምርቶች አቅርቦት መኖሩ ለግብይት አመቺ እንደሆነላቸው በመግለጽ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ሃና ዘሪሁን ገበያው ከሌሎች ገበያዎች ቅናሽ ያለው በመሆኑ በዚሁ ቢቀጥል ጥሩ ነው የዋጋ መረጋጋት ያመጣል ሲሉ ተናግረዋል።

በገበያው የሚፈልጉት ነገር ሁሉ ማግኘታቸውንና የዋጋ ቅናሽ መኖሩን የተናገሩት ደግሞ አቶ አበበ ኮምቤ ናቸው።

ወይዘሮ ዘነበወርቅ ሃይለስላሴ በበኩላቸው "የዋጋ ልዩነቱ፤አቅርቦቱ በጣም ቆንጆና የሚያስደስት ነው" ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው አምስተኛ ሣምንቱን በያዘው የእሑድ ገበያ 76 ያህል የሸማች ኅብረት ስራ ማኅበራት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁን የአምራች ሸማች የቀጥታ ገበያም ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈፀሙን ተናግረዋል።

የማኅበራቱን አቅም በማጠናከር የግብይት መዳረሻዎችን ቁጥር በማሳደግ በአምስት ክፍለ ከተሞች የተጀመረው የእሑድ ገበያ አሁን  በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የሸማች ኅብረት ስራ ማኅበራቱ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የዋጋ ንረትን የማረጋጋት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም