በመዲናዋ በስምንት መንግሥታዊ ተቋማት የዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ ሊጀመር ነው

66

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በስምንት መንግሥታዊ ተቋማት ከወረቀት ነጻ የሆነ የዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስፋት የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ።

ሥምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ "የስማርት ኦፊስ ፕላትፎርም" ፕሮጀክት ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።

እነዚህም ተቋማት፤ ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፣ ፋይናንስ ቢሮ፣ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃይል ልማት ቢሮ፣ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ሥራዎች ቢሮ፣ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና ገቢዎች ቢሮ ናቸው።

ፕሮጀክቱ በቀጣይ በመዲናዋ የሚገኙ በሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በቅድሚያ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ስምንት ተቋማት ባላቸው የተገልጋይ ብዛትና የአገልግሎት ስፋት አማካኝነት መመረጣቸው ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ እንዳሉት፤ በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈና ዘመናዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

እነዚህ ተቋማት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት መዘርጋት ሲጀምሩ  ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝና ሥርዓትን  በመዘርጋት ለተገልጋይን ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ተቋሙ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችላቸው በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም