የተከፈተብንን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ መክተን ልማታችንን እናረጋግጣለን

69

አዲስ አበባ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በመመከት ልማታችንን እናረጋግጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተውጣጡ የትምህርት ማሕበረሰብ አባላትና የፖሊስ አባላት በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰብል ሰብስበዋል።

በሰንዳፋ ከተማ አቅራቢያ በተደረገው የዘማች አርሶ አደሮች ሰብል ስብሰባ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል፡፡

May be an image of 2 people, people standing and grass

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ''ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ መሰባሰባችን ሁሉንም የሚያስመሰግን ነው'' ብለዋል።

ዘማች አርሶ አደሮች የኢትዮጵያን ነጻነትና ክብር ለማስቀጠል በግምባር አገር ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶችን  እየተፋለሙ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር ዘማቾች የሚከፍሉት መሰዋዕትነት ትልቅ ስፍራ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

የተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዘማቾቹን ሰብል መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ በኢኮኖሚ ግምባር የተከፈተውን ጦርነት መመከቻ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የከፈተውን የኢኮኖሚ ጦርነት ለመመከት በትጋት መስራት አለበት ብለዋል።

በዚህም  የኢትዮጵያ ብልጽግና፣ ልማትና ግንባታ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በዚህ በጎ ተግባር እንዲሳተፉ ትምህርት መዘጋቱን አስታውሰዋል።

በዛሬው እለትም ለዘማች አርሶ አደር ቤተሰቦች አለኝታና ድጋፍ ለማሳዬት ሰብል የመሰብሰብ ስራው በተሳካ መልኩ መከናወኑን አንስተዋል።

''እናንተ ብትዘምቱም እኛ አብረናችህ ቆመናል" የሚል ትልቅ የጋራ ስሜት በሚፈጥር መልኩ ስራው መከናወኑንም ነው የተናገሩት።

በሰብል ስብሰባው የተሳተፉ የትምህርትና የፖሊስ አባላትም በዚህ ስራ ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የህይወት ዋጋ ጭምር በመክፈል ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ዘብ የሆኑትን ዘማቾች መደገፍ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የትምህርቱ ማሕበረሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም