ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጎልበት ሀገርን ለማሻገር እንተጋለን

78

ድሬዳዋ፤ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በደም የተሳሰረ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ሀገርን ለማሻገር እንደሚተጉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ተሳታፊዎች ተናገሩ።

16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት በአስተናጋጇ ድሬዳዋ  በደም ልገሳ ተጀምሯል።

"ደም ያስተሳስራል"  በሚል መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ባለው ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሐራ ሁመድ እንደተናገሩት፤ ሀገርን ለማሻገር ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው ጀግናው መከላከያ ሠራዊት ደም መለገሱ በደም የተሣሠረ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ነው፡፡

ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወኪሎች የተለገሰው ደም አንድነትን በፀና መሠረት ላይ ይተክላል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የደም ልገሳው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ኃይል እያስመዘገበ ለሚገኘው ድል የደስታ መግለጫ ስጦታ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሣተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን፤ ደም በመለገስ የተጀመረው በዓል ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክርና ሀገር የማሻገሩን ዘመቻ ከግብ ለማድረስ መሠረታዊ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

ከደቡብ ክልል በበዓሉ ላይ የተገኙት ወይዘሮ መንደሪን ጌታሁን በበኩላቸው፤ ሀገርን እያሻገረ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት የሁሉም ብሔረሰቦች ተወካዮች ደም በመስጠት መተሳሰሩ ህብረ-ብሔራዊ አንድታችንን አፅንተን አገርን ለማሻገር የጎላ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

ከጀግናው ሠራዊታችን ጋር በደም መተሳሰርን በአንድነት የጀመርነውን ሀገር የማዳን ዘመቻና የደጀንነት ተልዕኮ ለማጠናከር ያግዛል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት ሁሴን ናቸው፡፡

ከደቡብ ኦሞ የመጣው ወጣት ኢርኖይ ዶሮች ፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት  ደም በመለገስ ብቻ ሳይሆን  በግንባር ከጎን በመሆን ኢትዮጵያን ለማሻገር በሚካሄደው እንቅስቅሴ የድርሻውን ለመወጣት  ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገረው።

በተመሣሣይ "ወንድማማችነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት"  በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔርብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዛሬ "ወጣትነቴን ለሀገሬ"ሃሳብ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶች የተሣተፉት ሲንፖዚየም ተጀምሯል፡፡

በሲንፖዚየሙ መድረክ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጭምር ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም