መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ለሰራዊቱና ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

86

ጎንደር ፤ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የሚገኙ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ተፈናቃይ ወገኖች 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደረቅ ስንቅና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ በርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ የተዘጋጀው ስንቅ ደጋፍ ያደረጉት የ110 ትምህርት ቤቶች መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ናቸው።

 280 ኩንታል በሶና ቆሎ፣ 414 ካርቶን ደረቅ ብስኩትና 2 ኩንታል ጫማ  ድጋፍ ከተደረው ስንቅ ውስጥም እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ ይህም 2 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ግምት አለው ብለዋል።

የትምህርት ቤቶቹ መምህራንና ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው ከ500 ብር ጀምሮ በነፍስ ወከፍ በማዋጣት የስንቅ ዝግጅን ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በአሽባሪው ህወሓት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 20 ኩንታል አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከ 2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለዘማች ቤተሰብ ተማሪዎችም 2 ሺህ 400 ደርዘን ደብተር፣ ለ23 ተማሪዎች ደግሞ በግልና በመንግስት ትምህርት ቤቶች ነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከሰሜን ጎንደር ዞን የተፈናቀሉ ከ3 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን በከተማው በሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንዲከታታሉ መመቻቸቱንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

ትውልድን በእውቀት፣ በስነ-ምግባርና በሀገር ፍቅር ስሜት ገንብቶ ከማውጣት ጀምሮ ሀገርን ለማዳን የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው  በመዝመት የድርሻቸውን መወጣታቸውን የገለጹት ደግሞ መምህር ብሩክ ሙላው ናቸው።

በጭና ግንባር ተሰልፈው አሸባሪው ህወሓትን በመፋለም ጉዳት ቢደርስባቸወም አገግመው ወደ ማስተማር ስራቸው መመለሳቸውን የጠቆሙት መምህር ብሩክ፤ ''ደጀን በመሆን ሀገሬን ከመደገፍ ወደ ኋላ አልልም'' ብለዋል።

በተጨማሪም በአሸባሪው ህወሓት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች በግላቸው አልባሳት መለገሳቸውንም  ተናግረዋል።

የከተማው መምህራን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከመቅረፅ ባለፈ ለህልውና ዘመቻው ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪና የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ በዛብህ ናቸው።

መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ከዚህ ቀደም የወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን አውስተው፤  ተጨማሪ የስንቅ ዝግጅት ማድረጋቸው በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን አመልክተዋል።

የጎንደር ከተማ ህዝብ የክተት ጥሪውን በመደገፍ በህዳር ወር ብቻ 114 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ 97 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደግሞ በዓይነት ድጋፍ ማደረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም