የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ገጽታ ለመገንባት በተለያዩ ቋንቋዎች የዲፕሎማሲ ሥራዎችን የማስፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል

56

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ገጽታ ለመገንባት በተለያዩ ቋንቋዎች የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማስፋት ሥራ ትኩረት መሰጠቱን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "የግጭት አዘጋገብና ዲፕሎማሲ" በሚል መሪ ሃሳብ በትላንትናው ዕለት የፓናል ውይይት አካሂዷል።  

በውይይቱ ዲፕሎማሲን በተመለከተ ጽሁፍ ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች መበርታታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የሐሰት መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን ለማስተካከል ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

አሁን አገሪቱ የገጠማት ችግርን የመከላከል ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የዲፕሎማሲ ሥራ ስኬታማ ለማድረግ በተለይም በዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተሳትፎ እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፍ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ገጽታዋን ለመገንባት በተለያዩ ቋንቋዎች የዲፕሎማሲ ሥራዋን የማስፋት ሥራ ትኩረት መሰጠቱን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል።  

መንግሥት ከሚያደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጎን ለጎን በተለይም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳያስፖራውን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሚኒስቴሩ የዲፕሎማቶች አቅም ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ንጋቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የማሳወቅና የማስገንዘብ ሥራ ሊጠናከር ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያ ጦርነት ለመቀልበስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።  

ሌላኛው የፓናሉ ተሳታፊ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሞሃመድ አል አሩሲም፤ ኢትዮጵያ የገጠማት ጫና ለመከላከል የዲጂታል ዲፕሎማሲ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያኖች የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት እንዳለባቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም ተደራሽነታቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች በማጠናከር ለአገራቸው ጉዳይ ልሳን ሊሆኑ እንደሚገባም ነው ምክረ ሃሳብ የሰጡት።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም