አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት የሚገቡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት እየተደረገ ነው

89

 ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ በመጪው የገና በዓል ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ምእራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያድርጉትን ሁሉን አቀፍ ጫና ለመመከት አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ወደ አገር ቤት በመትመም ሀገሪቷ ሰላም መሆኗን  እንዲያሳዩ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል።

ይሕንኑ ጥሪ ተከትሎም ዳያስፖራው ማህበረሰብ በፈረንጆቹ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ወይም የፊታችን ታህሳስ ወር መጨረሻ ወደ አገር ቤት ለመግባት እንዲችሉ ሰፊ ንቅናቄ  እያደረጉ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ ለኢዜአ እንዳሉት፤የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በአሸባሪው ቡድን እና በኮቪድ 19 የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍን ለማነቃቃት የዳያስፖራው ማሕበረሰብ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሄዱበት ሁሉ የአገራቸው አምባሳደር ሆነው በኢትዮጵያን የገጽታ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ታላቅ ዕድል እንደሚኖረው አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ውስጥ ቆይታቸው በቱሪስት መዳረሻዎች በመዘዋወር የኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዲጎበኙ ለማድረግም በቅንጅት እየተሰራ እንደሆን አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር ናሲሴ ገለጻ፤ ጉብኝቱ ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ባለፈ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን በተጨባጭ ለዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳየት ይረዳል ነው ያሉት ።

በተጨማሪም አንዳንድ የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ውትወታ ለማጋለጥ ያገዛል ነው ያሉት ።

ለዚሁም ስኬት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም የሆቴልና አገልግሎት ሰጭ ማህበራት የጉብኝቱን አገራዊ ፋይዳ በመረዳት በኃላፊነት እንዲሰሩ ከማድረግ አንፃር መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

ዳያስፖራው ኢትጵያን ጎብኝቶ መመለስ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የአገር ግንባታ ውስጥ በመሳተፍ  ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቤት ስራዎች እንዲሰሩ ጥረቶች ይደረጋሉ ብለዋል።

የዲያስፖራው ጉብኝት ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ በድሕረ ጦርነት በአገር መልሶ ግንባታ ሚና ይዘዋቸው የሚሄዱ የቤት ስራዎችን ለማስገንዘብ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይም ጉብኝቱ በውጭ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ባህል፣ ወግ፣ እደ ጥበብ እና የጋራ እሴቶችን ለማስተዋወቅ መልካም እድል እንደሚፈጠር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።

በተለይም በሌላው ዓለም የሚኖሩ እና ኢትዮጵያን በሚገባ የማያውቁ የዳያስፖራው ማሕበረሰብ አባላት ማንነታቸውን በቅርብ እንዲመለከቱና አገራቸውን እንዲደግፉ የሚያስችል እንደሚሆን ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳሬክተር አቶ እንድሪስ አብዱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ባህልና እሴታቸውን ለአለም እንዲያንጸባርቁ ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም