በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላሉ ባለሃብቶች አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው

97

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላሉ ባለሃብቶች አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት መንግስትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የፈቀደችው ከቀረጥ ነፃ እድልን ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም ለማድረግ ተገቢ ያልሆነ ጫና እየተደረገ ነው፡፡

በዚህም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሚሰሩ ባለሃብቶች ተጎጂ እንዳይሆኑ አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአግዋ መሰረዝ ምርት ማቆምና ሠራተኞችን መበተን አይደለም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ባለሃብቶቹ በአሜሪካ ገበያ ምርቶቻቸውን የሚልኩበት ሌሎች አማራጭን እያጤኑ መሆኑንም አመላክተዋል።

በአውሮፓና ሌሎች አገራት ያሉ የገበያ አማራጮችን መጠቀምም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የቀረጥና ኮታ ነጻ ገበያ እድል (አግዋ) አባልነት እንድትሰረዝ የተላለፈው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት መንግሥት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

መንግስት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የገበያ አማራጮችን ከማስፋት ባለፈ የምርት አይነትን ለመጨመር እየሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የሚገጥሙ ችግሮች ላይ ተመስርቶ ማሻሻያዎችን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም