በባሌ ዞን ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል መሰብሰብ ጀመሩ

75

ጎባ፤ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ 42 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል መሰብሰብ መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብርሃም ኃይሌ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት  የትምህርት ቤቶቹ  ተማሪዎችና መምህራን  ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የሰብል አሰባሰብ ዘመቻ ላይ ይሳተፋሉ።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ  42 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ 32 ሺህ ተማሪዎችና መምህራን በስራው መሳተፍ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በዚህም  የደረሰ የዘማች ቤተሰቦች   ሰብልን በህብረት የሚሰበሰቡ ሲሆን፤ ይህም በተማሪዎች መካከል የሀገር ፍቅር ስሜትና አንድነት ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተመልክቷል፡፡

ሀሰን መሐመድ  የጎባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ  ሲሆን፤ በሀገር ሉዓላዊነት መከበር ውስጥ አሻራችንን ለማኖር በሰብል አሰባሰብ  ዘመቻ እየተሳፍን ነው ሲል ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡

የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ሰሚራ አብዱሰመድ በበኩሏ፤ በዘመቻው  ለሀገራዊ ጥሪው ምላሽ ከመስጠት በተጓዳኝ ወንድማማችነትና አብሮነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግራለች፡፡

ዘመቻው የአንድነትና የመተባበር እሳቤን በተማሪዎች ውስጥ ለማስረጽ ጉልህ ድርሻ  እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ  የትምህርት ቤቱ መምህር ደረጀ ከበደ ናቸው።

በሲናና ወረዳ የኦቦራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ጌታሁን አዱኛ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያዊያን ከተባበረንና አንድ ከሆንን በሁሉም ግንባር አሸናፊ እንደምንሆን በማመን በዚህ ላይ አሻራዬን ለማኖር በዘማች ቤተሰብ ሰብል ስብሰባ ዘመቻው  መሳተፉን  ተናግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፤አርሶ አደሩን ማኅበረሰባችንን በሰብል ስብሰባ ለመደገፍ  ለተሠማራችሁ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በሙሉ አድናቆቴ ይድረሳችሁ፤ እንደ ሀገር በአንድነት ሆነን በጽናት ጉዟችንን እንቀጥላለን! ሲሉ መለዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም