ዩኒቨርሲቲው አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችን ተቀበለ

53

ጅማ፣ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ከ780 በላይ ተማሪዎችን ተቀበለ።
አሸባሪው ህወሓት በእብሪት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል እና በግፍ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘጋታቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ቆይተዋል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተቀበላቸው ተማሪዎችም በሽብር ቡድኑ ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ሲል በእብሪት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ ትምህርታቸውን አቋርጠው የቆዩ መሆናቸውም ተገልጻል።

ዩኒቨርሲቲው የተቀበላቸው ተማሪዎች አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከአክሱም፣ መቐለና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ያቋረጡ ናቸው።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ እንዳሉት ተማሪዎቹ በሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ሁሉ ዩኒቨርስቲው ከጎናቸው ሆኖ ይደግፋቸዋል።

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ከሁሉ በላይ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ዓላማቸውን እንዲያሳኩ መክረዋል።

ከነባር ተማሪዎች ጋር ተባብረው የሠላም አምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ናቸው።

ለተማሪዎቹ አስፈላጊው የምክር አገልግሎት እንዲያገኙና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ መደረጉንም ምክትል ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም