በኢትዮጵያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ በካሊፎርኒያ ግዛት ተሰበሰበ

172

 ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች በኢትዮጵያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገለጸ።

በቀጣይ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ይካሄዳሉ ተብሏል።

ትናንት በካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው ሳን ሆዜ ከተማ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች  የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡን ኢዜአ ከዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሳን ሆዜ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውንና ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸው ነው የተነገረው።

በመርሃ ግብሩ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ዳያስፖራዎችን ጨምሮ 400 የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኙ አራት ከተሞች ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ተካሄደዋል።

በዚህም በኦክላንድ 230 ሺህ፣በሳክራሜንቶ 250 ሺህ፣በሎስ አንጀለስ 640 ሺህ እና በሳን ሆዜ 300 ሺህ፤ በድምሩ 1 ሚሊዮን 420 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡን ኢዜአ ከመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በተያያዘም በሕዳር ወር 2014 ዓ.ም ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች በዳላስ ቴክሳስ 445 ሺህ እንዲሁም በኒው ዮርክ 200 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሰብስቧል።

በቀጣይ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች በካሊፎርኒያ፣አሪዞና፣ሚኒሶታና ቴክሳስ ግዛቶች እንደሚካሄዱ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም