የሶማሌ ክልልን የመንግስት መዋቅር ከላይ እስከታች የማደራጀት ስራ ይሰራል

86
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 የሶማሌ ክልልን የመንግስት መዋቅር ከላይ እስከታች የማደራጀት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴው ገለጸ። ማዕከላዊ ኮሚቴው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከነሀሴ 4 እስከ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ግምገማ ሲያካሂድ ቆይቶ ውጤታማ ውሳኔዎችን እና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎችም ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ውይይቶችን በማድረግ አጠናቋል፡፡ በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋሉ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እንደነበሩ በመገምገም በሁከት እና ብጥብጡ ሰበብ ለጠፋው ህይወት፣ ለተዘረፈው ንብረት፣ ለወደመው የሀገር ሀብት እና ከቀዬው እና ንብረቱ ለተፈናቀለው ሰላማዊ ህዝብም የሚጠየቀው አመራሩ እንደሆነ መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡ የክልሉ ሀብት እና ንብረት እጅግ ከፍተኛ በሆነ መልኩ እንደባከነ እና የህዝቡን ችግሮች በመሰረታዊነት መቅረፍ የሚችል ሀብት እንደዋዛ እንደጠፋ ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ይህ የመንግስትን ንብረት አለአግባብ የማባከን ጉደይ የመንግት ንብረትን ግለሰቦች ተካፍለው እስከመውሰድ በጥሬ ሀቁም እስከመዝረፍ የዘለቀ እንደሆነ በስፋት ተገምግሟል፡፡ በመሆኑም ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ መልካም አስተዳደር ለማስፈን የክልሉን መንግስት መዋቅር ከላይ እስከታች የማደራጀት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል። መረጃዎች ለህዝብ ግልጽ እንዲሆኑ እንደሚደረግና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁ የሀሰት ወሬዎችን እና አሉቧልታዎችን በመመልከት ህዝቡ እንዳይወናበድም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም