በተዓምር የተረፈች ህይወት ህያው ምስክርነት

88

በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በአሸባሪው ህወሓት ግፍና ስቃይ የደረሰባቸው የመንግስት ሠራተኛው ህያው ምስክርነት።

አንዳንዴ ሞት ቅርብ ይሆንና ብርቱ የሚባሉት ሳይቀሩ በትንታ አሊያም በእንቅፋት ሞቱ ሲባል ይሰማል። በድንገት በተቀመጡበት አሊያም እንደተኙ ህይወታቸው አለፈ የሚባል ልቦለድ መሰል ታሪክ የሚሰማበት አጋጣሚም አለ።

'አትሙቺ ያላት ነፍስ'…እንዲሉ የዛሬው ባለታሪክ ገጠመኝ ግን ከእዚህ በተቃራኒው ነው። ባለታሪኩ አቶ እምወደው ነጋሽ ይባላሉ። በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ጽህፈት ቤት የኦዲት አስተባባሪ ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት በእብሪት በወረራቸው አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎች በጭካኔ ገድሏል፤ አሰቃይቷል፤ለዘመናት ከኖሩበት፣ ወግ ማዕረግ ካዩበት ቄያቸው፣ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። ታዳጊ ሕፃናትን ሳይቀር ሴቶችን ደፍሯል፤የቻለውን ሀብት ንብረት ዘርፏል፤ ያልቻለውን አውድሟል፣ የእምነት ተቋማትን አርክሷል፤ አቃጥሏል።

አቶ እምወደውም የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ንጹሃን ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው። 'አትሙቺ ያላት ነፍስ' እንዲል ሀገራዊ ቢሂሉ ህይወታቸው በተዓምር ተርፋ ይኸው ዛሬ የሽብር ቡድኑ በንጽሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ግፍ፣ ስቃይና መከራ ህያው ምስክር ሆነዋል።

ባለታሪኩ ገጠመኛቸውን እንደተረኩት፤ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ህይወታቸውን ለመንጠቅ ከድብደባ ጀምሮ የጠብመንጃ አፈሙዝ ወድረው እስከ ማስፈራራትና ማሰቃየት የደረሱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሞባቸዋል።

ህይወታቸውን ለመንጠቅ የመሳሪያ ምላጭ ተስቦባቸዋል። ህይወታቸው ግን በተዓምር ተርፋለች። የሽብር ቡድኑ የጭካኔ ተግባር በታሪክ ተከትቦ ለትውልድ የሚቀመጥ የዘመኑ ጥቁር ጠባሳ ነውም ይላሉ።

የሽብር ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎችም የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት በንጹሃን ላይ አዕምሯዊ፣ ስነልቦናዊና አካላዊ ጠባሳ ጥሎ ስለማለፉ "ራሴ ህያው ምስክር ነኝ" ሲሉም ያክላሉ።

አቶ እምወደው ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጧት ከአንድ አዛውንት ጋር ተቀምጠው የሆድ የሆዳቸውን እያወጉ ሳለ በአካባቢው የጥይት ድምፅ ይሰማ ጀመር። ተኩሱ እየጨመረ ይመጣል። የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ሳያሰቡት ከአዛውንቱ ደጃፍ ደርሰው ወደ ቅጥር ጊቢው ይዘልቃሉ። አቶ እምወደውም ሳያስቡት ከታጣቂዎቹ እጅ ይወድቃሉ። የአሸባሪው ታጣቂዎች ቀበቷቸውን አስፈትተው፣ ጫማቸውን እና የጣት ቀለበታቸውን አስወልቀው፤ ኪሳቸውን በርብረው ያገኙትን ቤሳ ቤስቲን  ሳይቀር ይወስዳሉ።

በዚህም ሳያበቁ ይዘውት በነበረው አካፋ፣ ዱላና  በክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ሰደፍ እየተፈራረቁ በጭካኔ እንዳይሞቱ እንዳይሽሩ አድርገው ነርተዋቸዋል፤ አሰቃይተዋቸዋልም። የብሬንና የዲሽቃ ጥይት በጀርባቸው አሳዝለው፣ በትከሻቸው አሸክመው በባዶ እግራቸው ረጅም መንገድ ይዘዋቸው ተጉዘዋል። በጉዞ ላይ እንዳሉም ድብደባው አልቀረላቸውም። በወቅቱ የደረሰባቸውን ስቃይና እንግልት እንዲህ ሲሉ ነው በአንደበታቸው የገለጹት።

 "ከታጣቂዎቹ አንደኛው አንበርክኮ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ አፈሙዝ ደቅኖ አሰቃይቶኟል።ብቻ ህይወቴ  የተረፈው በተአምር ነው። ሰውነቴ በደረሰብኝ ድብደባ ላሽቋል፤ መታዘዝ ተስኖታል።" ታጣቂዎቹ በመኪናቸው ላይ እንዲወጡ ያዟቸዋል። በድብደባው ላሽቆ የዛለው ወገባቸው፣ እግር እጃቸው ግን ሊታዘዛቸው አልቻለም። በዚህም የተነሳ የተባሉትን መፈጸም ተሳናቸው። መኪናው ላይ ለመውጣት ያለ የሌለ ሃይላቸውን አሰባስበው ተፍጨረጨሩ ግን አልቻሉም። የጥረታቸው ውጤት መልሶ መላልሶ ከአስፋልት መንገድ  ላይ  መውደቅ ብቻ ሆነ። በዚህ ስቃያቸው የተናደደው ሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች አለቃ በንዴት ጦፎ ያብዳል።እና “በመኪና ሂድበት” የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል። ይህን የሰሙት አቶ እምወደው የቀራቸውን እንጥፍጣፊ አቅም አሟጠው ያንገላቷቸው በነበሩት ታጣቂዎች እየተጎሸሙ፣ ተወርውረው መኪናው ላይ ያርፋሉ። ታጣቂዎቹ አሁንም እየተቀባበሉ ከላይ፤ ታች እንደ ቅሪላ እየነረቱ እንደ አሰቃዩዋቸው ይተርካሉ።

በአሳር በመከራ መኪናው ላይ እንደወጡ አንደኛው ታጣቂ ሽጉጥ አፈሙዝ ግንባራቸውን መቶ ያንበረክካቸዋል። በዚህ ሳያበቃ ካንበረከካቸው በኋላ ሽንቱን ግንባራቸው ላይ ይሸናል። “ተንበርከክ ሲሉኝ የጠበኩት ሞት ነበር” ሲሉ ነው ሁኔታውን ለማስታወስ በዝምታ የኋልዮሽ በሃሳብ የነጎዱት። ሴቶቻቸው ጭምር ማንነታቸውን የሚያጎድፍ ክብረነክ ቃላትን ተጠቅመው እንደ አዋረዷቸው ይገልጻሉ። በጭካኔ በትራቸው በማድቀቃቸው ስላልረኩ ድንገት ሳያስቡት ቀኝ እጃቸውን መርፌ ይወጓቸዋል። ከዚያ በኋላ እንቅልፍ ስለወሰዳቸው የሆኑትን አያውቅም፤ አሁንም አያስታውሱትም። ከመኪናው ጠርዝ ላይ አስተኝተዋቸው ሲወጡና ሲወርዱ መረማመጃ አድርገው ረጋግጠው አሰቃይተዋቸዋል። ስቃያቸውን እንዲህ ያስታውሱታል።

"አንደኛው ታጣቂ ጩቤ አውጥቶ አንዴ አንገቴ ላይ፣ ሌላ ጊዜ ከንፈሬ ላይና ሆዴ አካባቢ በማስጠጋት እየዛተ ለመሰንዘር ሲቃጣ ተስፋ ቆረጥኩ፤ መሞቴን አምኜ ሬሳዬን የት እንደሚጥሉት ብቻ ነበር ሳስብ የነበረው" ይላሉ አቶ እምወደው፣ "አይና" ከተማ እንደገቡ በማግስቱ እንዲገደሉ ተወሰነ። የሚቀበሩበትን ጉድጓድም ራሳቸው እንዲቆፍሩ ትእዛዝ ተላለፈ ሲሉ ሁኔታውን እንዲህ ይተርካሉ።

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በግፍ የፈጸሙባቸውን የጭካኔ ተግባር ሲያስታውሱት አሁንም ይዘገንናቸዋል። አፍረተ ሥጋቸውን ጨምሮ በአካላቸው ላይ ያደረሱባቸው ጉዳት ለስነልቦና ችግር ዳርጓቸዋል።

በቀኝ እጃቸውና በመቀመጫቸው ላይ የወጓቸው መርፌ ምን እንደሆነ በሕክምና ማረጋገጥ ስላልቻሉ ሰላም ነስቷቸዋል። 'ትረፊ ያላት ነፍስ' እንዲል ሀገራዊ ቢሂሉ አቶ እምወደው በተአምር ከሞት ተርፈው ዛሬ ታሪክ ነጋሪ ሆነዋል። አሸባሪው ህወሓት በንጽሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ህያው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በሽብር ቡድኑ የግፍና የጭካኔ ድርጊት ህይወታቸው እንደ ዋዛ የተቀጠፈ ወገኖቻችንን  ቤት ይቁጠራቸው ሲሉ የደረሰባቸውን ስቃይና እንግልት ቋጭተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም