ሁሉም ዜጋ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ትግሉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል

104

አርባ ምንጭ፣ ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሁሉም ዜጋ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ትግሉ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ የምሁራን ውይይት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አስተባባሪ አቶ ኃይለሚካኤል ደቢሳ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ጂኦፖለቲካ አንፃር በየጊዜው የዲፕሎማሲ ጫና ይደርስባታል።

በኢትዮጵያ ከተካሄዱ ጦርነቶች በስተጀርባ የዓባይ ውሃ እንዳለ ጠቁመው በፋሺስት የጣሊያን ወረራም እንግሊዝ የጦርነቱ ጠንሳሽ እንደነበረች አስታውሰዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን የማደግ መብት ለመገደብ ከግብፅ፣ ከሱዳንና ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በመሰለፍ ማሴራቸው ወቅቱን አይመጥንም፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳንገድብና የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ተጽኖ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው፣ "አሁንም ግድቡ ሃይል ማመንጨት እንዳይጀምር ኢትዮጵያ አስገዳጅ ፈርማ አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ እየጣሩ ናቸው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ቀጠና አገር እንደመሆኗ መጠን ከቀጠናው ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ያልተገባ ተጽዕኖ ለማሳደር እየጣሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አገራቱ የነፃነትና የጥቁር ህዝቦች ምሳሌ የሆነችውን ኢትዮጵያን በማዳከም አፍሪካን ዳግም በቅኝ ለመግዛት መቋመጣቸውን ያስታወሱት አስተባባሪው፣ ሁሉም በዲጅታል ዲፕሎማሲው የአገሩ አምባሳደር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩና የዓባይ ውሃ ተደራዳሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላትና የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን ገልጸዋል።

በቅኝ አገዛዝ ዘመን ጊዜ በርሊን ላይ ተቀምጠው አፍሪካን የተከፋፈሉ ምዕራባዊያንና አሜሪካ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ባልተገባ መንገድ የግብፅና ሱዳን ጉዳይ አስፈጻሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በእዚህም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸው ሳያንስ በአሁኑ ወቅትም ከህወሓት የሽብር ቡድን ጋር መሰለፋቸው አስነዋሪ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአገሯ ያለውን አንጡራ ሀብት ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባትም ዶክተር ያዕቆብ አስገንዝበዋል።

"የኢትዮጵያን እውነታ ለማስገንዘብ የመንግስት የዲፕሎማሲ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ በዲጅታል ዲፕሎማሲው ሁሉም የአገሩ አምባሳደር ሊሆን ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የገጠሙ የውጭና የውስጥ ፈተናዎች በዕድገት ደረጃዋ ላይ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በአሁኑ ወቅት ዜጎች በያሉበት እውነታውን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት በመመስረት ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጉዳትና የአፍሪካን ሀብት ለመቀራመት የሚደረግ ማንኛውም የአሜሪካና የምዕራባዊያን ሙከራ አይሳካም" ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባላቸው አጋጣሚ በመጠቀም በዲጂታል ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይገባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ አሜሪካና ምዕራባዊያን በአፍሪካ ቀንድ ባላቸው ፍላጎትና በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩም የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም