ኢትዮጵያን በሚመለከት በተለያዩ መንገዶች እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጻረሩ ናቸው

56

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በሚመለከት በአንዳንድ አካላት እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጻረሩ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የህግ ባለሙያዎች እንዳሉት በተለይ አሁን ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከእውነታው የራቁና የተዛቡ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ይስተዋላል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪው ሞላልኝ መለሰ፤ ኢትዮጵያን በተመለከተ እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጻረሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በመሆኑም በየትኛውም የሚዲያ አማራጭ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ያሉ አካላት ወንጀል እየፈጸሙ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህ ወንጀል እየተሳተፉ ያሉ አካላትን ተከታትሎ ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፤ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት መሰረት አያሌው፤ የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ አካላትን በመቆጣጠር ረገድ ክፍተት በመኖሩ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ይናገራሉ።

ችግሩን ለመፍታት የመንግሥት አካላት፣ የሕግ ባለሙያዎችና ማኅበረሰቡ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፍ ሕጉንና ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሥምምነት ተከትሎ መንግስት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።

መንግስት ወንጀልን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት ጋር የገባውን ስምምነትና ትብብር መሰረት በማድረግ በየትኛውም አገር ሆነው ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን የሚያሰራጩ አካላት ላይ ክስ መመስረት ይችላል ሲሉም አስረድተዋል።

ለዚህም ደግሞ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ከመንግስት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም