ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊት አብሮ በመዝመትም በመደገፍም የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል

64

ህዳር 27/2014/ኢዜአ/ ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊት አብሮ በመዝመትም በመደገፍም የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሰራተኞች ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት በዛሬው እለት ደማቸውን ለግሰዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ፤ ኢትዮጵያ የተከፈተባት ጦርነት ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችም የተካተቱበት በመሆኑ ህልውናዋን ለማረጋገጥ በሁሉም ግንባር መሰለፍ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ ህይወታቸውን እየከፈሉ ላሉ የሰራዊት አባላት ያለንን አጋርነት ለመግለፅ የደም ልገሳ አድርገናል፤ ሌሎች ድጋፍና እገዛዎችንም እንቀጥላለን ብለዋል።

ከህልውና ዘመቻው ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በተሰለፉበት ሙያ ስኬት ከማስመዝገብ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቀ ላለው ሰራዊት የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ሲሆኑ በዛሬው እለትም ደማቸውን ለግሰዋል።

ከደም ለጋሾቹ መካከል ወይዘሪት ሰዓዳ መሀመድ እና አቶ መስፍን ታደሰ ደማቸውን ለጀግናው ሰራዊት በመለገሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊት አብሮ በመዝመትም በመደገፍም የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ ያለው አሸባሪው ህወሃት እስከሚወገድ ድረስ በድጋፍም፤ በመዝመትም እናግዛለን ያሉት ደግሞ ሌላኛው የኮርፖሬሽኑ ሰራተኛ አቶ ተካበ መኩሪያ ናቸው።

የጋራ አንድነትን በመጠበቅ፣ ጠንክሮ በመስራትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሁላችንም የህልውና ዘመቻው አካል መሆን አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም