የአቃቂ ቃሊቲ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት 48 ሚሊየን ብር የሚገመት የስንቅ ድጋፍ አደረጉ

112

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የአቃቂ ቃሊቲ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት 48 ሚልየን ብር የሚገመት የስንቅ ድጋፍ አደረጉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፎች እንዲሁም የማአድ ማጋራትና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ይገኛል።

በዛሬው እለትም የአቃቂ ቃሊቲ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት በድምሩ 48 ሚሊዮን ብር የሚገመት የስንቅ ድጋፍ አድርገዋል።

ከተደረገው ድጋፍ 30 ሚሊየኑን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያበረከተ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነው።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በስንቅ ዝግጅት ላይ ያገኘናቸው አቶ አባተ ዘሪሁን እና ወይዘሮ ትዕግስት በርጩማ ለሰራዊታችን ደጋፊ፣ አጋዥና ደጀን በመሆን የድርሻችንን እየተወጣን ነው፤ አጠናክረንም እንቀጥላለን ብለዋል።

የአቃቂ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ባለሃብቶችን፣ የመንግስት ሰራተኞችንና ነዋሪዎችን በማስተባበር በሶስት ዙር በገንዘብ እና በአይነት ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰበሰብ እንደተቻለ አስታውሰዋል።

በዛሬው እለትም ስንቅ በማዘጋጀት በግንባር ለሚገኘው ሰራዊታችን ለማድረስ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ የስንቅ ዝግጅት ማድረጉ ተገልጻል።

ከስንቅ አዘጋጆቹ መካከል ወይዘሮ ሸምሲያ አብዱ፤ ሰራዊቱ ለአገሩ ሲፋለም እኛም የቻልነውን ሁሉ እገዛና ድጋፍ እናደርጋለን፤ እያደረግንም እንገኛለን ብለዋል።

የአገራችን ጠላቶች እስኪጠፉ ድረስ በድጋፉ እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰናይት ብርሃኑ ናቸው፡፡

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቆንጅት ደበላ፤ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች 18 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት በማሰባሰብ ለመከላከያ ሰራዊት የማዕድ ማጋራት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

አሁንም የስንቅ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል ።

ወይዘሮ ቆንጅት ክፍለ ከተማው የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ በሁለት ዙር  ከ100 ሚሊየን ብር የሚበልጥ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም