ለአገርና ለህዝብ ክብር ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን- ባለሀብቶች

149

ጎንደር ህዳር 27/2014 ( (ኢዜአ) ለሀገርና ለህዝብ ክብርና ነጻነት ስንል ሀብትና ንብረታችንን ብቻ ሳይሆን ህይወታችንን ለመስጠት ዝግጁ ነን ሲሉ በአማራ ክልል ባለሀብቶች አስታወቁ፡፡

"የአንድነት ደወል ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ ለህልውና ዘመቻው ለቀረበ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በክልሉ ባለሀብቶች የተዘጋጀ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል ።

ከባለሀብቶቹ መካከል አቶ በላይነህ ክንዴ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ባለሀብቱ የህወሓት የሽብር ቡድን የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ ለሚፋለው ሠራዊት ለሀብቱ ሳይሳሳ እየደገፈ ይገኛል።

ወራሪው ሃይል በአማራ ክልል የልማት ተቋማትን በማፈራረስና ንፁሀንን በመግደል የፈጸመው እኩይ ተግባር ታሪክ ይቅር የማይለው አጸያፊ ድርጊት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

"የክልሉ ባለሀብቶች  ወረራውን ለመቀልበስ የጸጥታ አካላት እያደረጉ ያለውን የጀግንነት ተጋድሎ በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ የጀመርነውን እገዛ እናጠናክራለን" ሲሉ አክለዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ባለሀብቶች በመደራጀት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

''በህልውናችን፣ በእድገታችንና በልማታችን ላይ የመጣውን አሸባሪ ቡድን እጃችንን አጣጥፈን የምንጠብቅበት ምንም ምክንያት የለም" ያሉት ደግሞ የአማራ ባለሀብቶች አስተባባሪ አቶ ተካ አስፋው ናቸው፡፡

ሀብትና ንብረትን ከአገር ነጻነት በፊት የሚያስቀድም ባለሀብት እንደማይኖር ገልጸው "አገርን ጠብቆ ለትውልድ ለማስረከብ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ ነን" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ከአገሩ ሸሽቶ የወጣ የክልሉ ተወላጅ ባለሀብት እንደሌለ ጠቅሰው  ሀብትና ንብረት ላፈሩበት አገር ማናቸውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደ ኋላ እንደማይሉ አመልክተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ባለሀብቶች አስተባባሪ አቶ እስማኤል ኑር ሁሴን በበኩላቸው "ተላላኪና ቅጥረኛው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት በታሪክ የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ ነው" ብለዋል።

"ከፊት የተሰለፈ የአገር መሪ በታሪክ ድል እንጂ ሽንፈት ገጥሞት አያውቅም'' ያሉት አቶ እስማኤል፣ በግንባር ለዘመቱት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ታላቅ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል።

"እኛ ባለሀብቶች እስከ ድሉ መጨረሻ ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፋ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ባለሀብቶች ለህልውና ዘመቻው እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ በኢትዮጵያዊ አንድነት ስሜት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ለንግዱ ማህበረሰብ ከቀረቡ የመታሰቢያ ፎቶ ግራፎች ጨረታ ለህልውና ዘመቻው 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡፡

አቶ በላይነህ ክንዴ በህወሀትወራሪ ሃይል እናቱ የተገደሉበትን አንድ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ህጻን ተንከባክቦ ለማሳደግ ቃል በመግባት ታዳጊውን ተረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም