በዛቻና ማስፈራሪያ የሀገር ሉአላዊነት ለድርድር አይቀርብም - ወጣቶች

68

ነገሌ ህዳር 27/2014(ኢዜአ)  በኢኮኖሚ አሻጥር፣ በዛቻና ማስፈራሪያ የሀገር ሉአላዊነት ለድርድር አይቀርብም ሲሉ የጉጂ ዞን ወጣቶች ገለጹ፡፡
"ወጣቶቹ የኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ መነሳት የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን አስፈርቷል" ሲሉም ለኢዜአ  ተናግረዋል።

ከዞኑ ወጣቶች መካከል የአዶላ ሬዴ ወረዳ ነዋሪ ታሪኩ ኡቱራ እንዳለው እሱና ጓደኞቹ በግንባር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሰለፍ ሽብርተኛውን ህወሀት ለመፋለም ወስነዋል፡፡  

"የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችም ሽብርተኞችን በመደገፍና ኢትዮጵያዊያንን በማስፈራራት ሀገር ማፍረስ እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል" ብሏል ።

"በሽብር ቡድኖች ሀገር ሲፈርስ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ የሞራልም የታሪክም ተጠያቂ ያደርጋል" ያለው ደግሞ የነገሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፍሮምሳ ገመዳ ነው ።

የሽብር ቡድኖችን በሚደግፉ ምእራባዊያንና በመገናኛ ብዙሀኖቻቸው የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲሁም በዛቻና ማስፈራሪያ የሀገር ክብርና ሉአላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብ አመልክቷል፡፡   

ሽብርተኛው ህወሀትን በመጋለብ ሀገር ለማፍረስ የቋመጡ የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን የሀሰት ዘገባዎችን በማጋለጥ ሴራቸውን ለማክሸፍ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል ።

"በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመራር በሽብርተኛው ህወሀት ወራሪ ሀይል ላይ እየተመዘገበ ባለው ድል ኩራት ተሰምቶኛል፤ በግንባር ተሰልፌ የድሉ ተካፋይ እሆናለሁ" ሲል ወጣት  ፍሮምሳ አቋሙን ገልጿል ።

በዞኑ የጎሮ ዶላ ነዋሪ ወጣት ዘኪ አብዲ በበኩሉ በግንባር መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል  የሀገርን ህልውና ለማስከበር መወሰኑን ተኗግሯል።

"የውስጥና የውጭ ሽብርተኞችን ለመመከት የህይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ለሀገሬ አዲስ ታሪክ የምሰራበት ወቅት አሁን ነው" ብሏል፡፡

ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያዊያን ሉአላዊነታችንን ለማስከበር በአንድነት በመነሳታችን ሀገር ለማፍረስ  ያሰፈሰፉ የውስጥና ጨውጭ ጠላቶች ደንግጠዋል ።

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ "በደረቀ ጭንቅላትና አስተሳሰብ ሀገር ለማፍረስ የተነሳ የሽብር ቡድን መቼም ቢሆን አይሳካለትም" ብለዋል፡፡

"ወጣቶች ተነሱ፤ አከባቢያችሁን ጠብቁ፤ ዝመቱ፤ ሀገራችሁንም ከውርደት አድኑ፤ የአባቶቻችሁን የጀግነነት የታሪክ አደራ ከግብ አድርሱ" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም