ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነታችንን በማጠናከር የህልውና ዘመቻ ማሳካት ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል

78

ሐረር፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነታችንን በማጠናከር የህልውና ዘመቻውን ስኬታማ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ አመለከቱ።
16ኛው የኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በሐረሪ ክልል ደረጃ ዛሬ በተከበረበት ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ ባደረጉት ንግግር፤ "በወንድማማችነት፣ በአብሮነት እና በአንድነት የገጠመንን ሀገራዊ ፈተና ለማለፍ እኛ የኢትዮጵያዊያን በጋራ  እየመከትን እንገኛለን ብለዋል።

ሀገርን ለማፍረስ እና ትውልድን ለማጥፋት የመጣውን አሸባሪው ህውሃት እና ተላላኪዎቹ በጋራ በመከላከል የሚጠበቅብንን ሁሉ በተግባር እያሳያ ነው ሲሉ አክለዋል።

በአሸባሪው ቡድን የተፈናቀሉና የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ እየተዋደቁ ያሉ ዜጎች በመደገፍ እና በማገዝ ወንድማማችነትን ይበልጥ ማሳየት አለብን ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ፈተናውን ለመሻገር እና ብልጽግናችንን እውን ለማድረግ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነታችንን በማጠናከር የህልውና ዘመቻውን ስኬታማ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ሀገርን ለማፍረስ የተነሱ የውስጥም የውጭም ሃይሎችን በጋራ በመመከት ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።

“ዘመቻ ለሕብረብሔራዊ አንድነት” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሚመራው ዘመቻ የጠላትን ሃይል እየበታተነ እና አበረታች ድል እየተገኘ መሆኑንም አውስተዋል።

በክልሉም የተጀመሩ የሰላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎችም በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ  የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሁሉም የክልሉ አመራር እና ነዋሪዎች በተሰለፉበት ግንባር ሚናቸውን ማጎልበት ይጠበቅብናል ሲሉም አብራርተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም በበኩላቸው፤ በዓሉ ዘንድሮ ልዩ የሚያደርገው ሀገርን ለማዳን ወደ ግንባር ዘምተው ሰራዊቱን በመምራት ከጠላት ጋር እየተፋለሙ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀግንነት አመራር የታየበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።

ሀገርን ለማፍረስ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች እኩይ ተግባር ለመመከት የኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያሳዩት አንድነትን የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ሰራዊቱን ከመደገፍ አንጻር እየተከናወነ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

"ወንድማማችነት ለሕብረብሔራዊ አንድነት" መሪ ሀሳብ በክልሉ ምክር ቤት በተከበረው በዓል ላይ  "የሀገርን ህልውና በማስከበር የኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሚና" በሚል  ርዕስ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ተሳታፊዎቹም ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም