የጋምቤላ ክልል በአሸባሪው ወረራ ተፈናቅለው ድጋፍ ለሚሹ የአፋር ክልል ወገኖች ድጋፍ አደረገ

72

አዲስ አበባ ህዳር 27/2014(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ተፈናቅለው ድጋፍ ለሚሹ የአፋር ክልል ወገኖች ሶስት ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ አደረገ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ኡጁሉ የተመራው ልዑክ ድጋፉን ለማድረስ ሰመራ ሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ አየር ማረፊያ ሲደርስ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል።

አቶ ዑመድ ኡጁሉ፤ የጋምቤላ እና የአፋር ክልል ሕዝቦች የጭቆና ቀንበር ተጭኖባቸው በአገራቸው ጉዳይ እንዳይወስኑ ሲደረግ ነበር ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የጭቆናው ቀንበር ተገርስሶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በአገራቸው ጉዳይ ባለቤት መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።

መንግስት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ ያሳለፈውን የተኩስ አቁም ውሳኔ የተወው የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ዜጎችን ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ መዳረጉን አንስተዋል።

በመሆኑን ከአፋር ወገናችን ጎን መሆናችንን ለማሳየት ሶስት ሚሊዮን ብር፣ አልባሳት እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ የአፋር ሕዝብ ችግር በገጠመው ጊዜ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ችግሩን በጋራ ለማለፍ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ "ምስጋና አቀርባለሁ" ብለዋል።

ወራሪው ህወሃት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ደጀን ሕዝብ ይዞ ድል እየተቀዳጀ የሚገኘውን ሠራዊት በመዘንጋት በፈጸመው ወረራና ጦርነት የእጁን እያገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በቢሊዮን ብር የሚጠጋ የሕዝብና የመንግስት ሃብትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም