አሸባሪው ህወሃት ሽንፈቱን በማህበራዊ ትሰስር ገጾች አዛብቶ በማቅረብ ለማደናገር እየሞከረ ነው

195

ህዳር 25/2014 /ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሃት በግንባር እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት በማህበራዊ ትሰስር ገጾች አዛብቶ በማቅረብ ለማደናገር እየሞከረ መሆኑን የማህበራዊ ሚዲያ ዲዛይነርና የዲጂታል ኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር አብዮት ባዩ  ተናገሩ።

የአሸባሪውን እኩይ አላማ በአግባቡ በመረዳት ህብረተሰቡ ያልተረጋገጡና ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎችን አለመጠቀምና አለማጋራት እንደሚገባውም መክረዋል።

አሸባሪው ህወሃት በጦር ግንባር እየተሸነፈ በመሆኑ ሌሎች የማደናገሪያ አማራጮችን እየተጠቀመ መሆኑንም ዶክተር አብዮት ተናግረዋል ።

በመሆኑም አሸባሪው ሃይል በግንባር እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት በማህበራዊ ትስስር ገጾች አዛብቶ በማቅረብ ህዝብ ለማደናገር እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ አሸባሪው የሚያሰራጨው የተሳሳተና ሀሰተኛ ወሬ ለአንዳንዶች እውነት ስለሚመስላቸው ሲደናገሩ ይስተዋላል።

የአሸባሪ ቡድኑ ተላላኪዎችና ጥቅመኞች በዲጅታል ሚዲያው በሚያሰራጩት ዘመቻ ሳንደናገርና  ሳንዘናጋ በጋራ ልንመክት ይገባል ብለዋል።

ከጠላት የሚሰነዘረውን የተዛባ የመረጃ ጦርነት በአንድነት መዋጋትና እውነታውን በተለያዩ አጋጣሚዎች በማሳወቅ ለአገራችን ህልውና አብረን ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።

የጠላት ሃይል የሚያስተላልፋቸው መረጃዎች በፈጠራ ታግዞ በድምጽና ምስል አቀነባብሮ በመሆኑ ምንጫቸው የማይታወቁና የሚያጠራጥሩ መረጃዎች ሊያደናግሩን ለሌሎችም ልናጋራቸው አይገባም ብለዋል ዶክተር አብዮት።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተለያዩ አውደ ግንባሮች ሃይል አሰልፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም ግንባሮች ድል ለማድረግ የጋራ ክንዳችን ያስፈልጋል ብለዋል።

አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃንም ኢትዮጵያን በሚመለከት የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ለአገራችን ሉአላዊነትና ጥቅም ሁላችንም መከታና ጠበቃ ሆነን መገኘት አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ጉዳይ አብሮ የሚቆምበት ወሳኝ ጊዜ አሁን በመሆኑ ለሁሉም ግንባር አሸናፊ ለመሆን እንዘጋጅ ብለዋል።

መንግስትም መረጃን በፍጥነትና በአንድ ቋት ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል በማለት ዶክተር አብዮት አስገንዝበዋል።