የህግ አሰራር ሂደቶችን ዜጎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን የሚከታተሉበት አሰራር ሊጀመር ነው

188

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የህግ አሰራር ሂደቶችን ዜጎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን የሚከታተሉበት ዘመናዊ የመረጃ አቅርቦትና የአሰራር ስርአት ሊጀመር መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

የወንጀል ምዝገባ አስተዳደር ስርዓትን በተመለከተ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና በሚኒስቴሩ ስር ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

በፍትህ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ፋንታዬ ኩምሳ፤ የወንጀል መዛግብትን የመረጃ አያያዝን ለማዘመን የወንጀል ምዝገባ አስተዳደር ስርዓት ፕሮጀክት መቀረፁን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቴክኖሎጂ የማልማት የሙከራ ትግበራ እንዲሁም የፍተሻ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

አሁን ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አሰራሩ ጥቆማን ከመቀበል ጀምሮ ምርመራን ማደራጀት፣ የክስ መመስረትና ሌሎች የፍርድ ቤት ሂደቶችን መመዝገብ ያስችላል ብለዋል።

የመረጃ ስርዓቱ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራር መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የፍርድ ቤትና የህግ አሰራር ሂደቶችን ዜጎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን የሚከታተሉበት ዘመናዊ አሰራር ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የመረጃ ስርዓቱን በተመለከተ ለፌዴራል ፖሊስ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው በፍትህ ሚኒስቴር ስር ላሉ የሚመለከታቸው አካላትም ተመሳሳይ ሥልጠና በመሰጠት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመረጃ ስርዓቱ በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የመረጃ አሰራር ስርዓቱን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ከክልል ከተሞችም በድሬደዋና ሀዋሳ ይጀመራል ተብሏል።