ተጓዦች በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ለሚደረገው ፍተሻ አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ ነው

170

ህዳር 25/2014 /ኢዜአ/ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች የሚደረገው ቁጥጥርና ፍተሻ የጋራ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መንገደኞችና የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ገለጹ።

ተጓዦች የፍተሻ እና ቁጥጥሩን ዓላማ በመረዳት አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ መሆኑም ተነግሯል።

ተግባራዊ በተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ ጥብቅ ፍተሻና ክትትል እንዲደረግ የሚያዝ መመሪያ ተቀምጧል።

በዚሁ መሰረት በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች የመንገደኞችን ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ ማየትና ፍተሻ በማድረግ መንገደኞች ያለ ምንም ስጋት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል።

ኢዜአ በአዲስ አበባ ላምበረት መናኸሪያ ተገኝቶ የሚደረገውን ቁጥጥርና ፍተሻ በመቃኘት መንገደኞችና አሽከርካሪዎችን አነጋግሯል።

ተሳፋሪዎችን ይዘው ወደ ሐዋሳ ለመጓዝ የተዘጋጁት አሽከርካሪ አቶ ጸጋ አዳነ፤ መንገደኞች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ አሳይተውና የያዙት ዕቃ ተፈትሾ ወደ ተሽከርካሪው እንደሚገቡ ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ አሽከርካሪውም ሆነ ተሳፋሪዎች ከስጋት ነጻ ሆነው አንዲጓዙ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

በመናኸሪያው መግቢያ በር ላይ ከሚደረገው ፍተሻ በተጨማሪ አሸከርካሪው የመንገደኞችን መታወቂያ የማየትና የማረጋገጥ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፍተሻ የሚደረገው ለጋራ ደህንነት መሆኑን በመገንዘብ ተሳፋሪዎችም በፈቃደኝነት ትብብር እያደረጉ መሆኑን  አክለዋል።

ሌላው አሽከርካሪ አቶ ኤፍሬም አርጋሙ፤ ፍተሻ መደረጉ መንገደኞች ምንም ስጋት ሳይሰማቸው የሚፈልጉበት ቦታ መድረስ እያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በጉዞ ላይም እንዲሁ በተለያዩ ቦታዎች ፍተሻ መኖሩ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ ክትትል በማድረግና በመለየት የኅብረተሰቡን ደህንነት የማስጠበቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

መንገደኞች በበኩላቸው በጉዞ ላይ ሰርጎ ገቦች በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከል በመናኸሪያዎች የተጀመረው የፍተሻ ስርዓት የተቃና እንዲሆን መተባበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ወጣት አስማማው ሺመልስ ፍተሻ መኖሩ ሁሉም ደህንነቱ ተጠብቆና ተረጋግቶ እንዲጓዝ ያደርጋል ብሏል።

የፌዴራል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመናኸሪያ አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ታምራት ለገሰ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ችግር እንዳይፈጠር እየተሰራ ነው ይላሉ።

ተጓዞች ወደ መናኸሪያ ሲገቡ አስፈላጊውን ፍተሻ በማካሄድና ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያሳዩ በማድረግ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

አብዛኛው ተጓዥ የፍተሻውን ዓላማ በመረዳት አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፍተሻ  ስራው ተጠናቀሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።