በ "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" የኢትዮጵያ አሸናፊነት ይረጋገጣል

67

ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በ "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" የኢትዮጵያ አሸናፊነት ይረጋገጣል ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።

ለኢትዮጵያ አሸናፊነት የአራቱም ማዕዘናት ልጆቿ ብርቱ የአንድነት ንቅናቄ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ተናግሯል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በአፋር ክልል በመገኘት በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ከጭፍራ ከተማ ተፈናቅለው ለሰብዓዊ ቀውስ ለተጋለጡ ዜጎች የሚውል ድጋፍ አበርክቷል።

ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በሃምሳ መጠለያ ጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙ ተፈናቃዮችናንና በሽብር ቡድኑ ውድመት የደረሰበትን የጭፍራ ከተማም ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጸውም በጭፍራ ከተማ መገኘቱ ሁለት አይነት ተቃራኒ ስሜት ፈጥሮበታል።

ይኸውም የወገን ጦር በሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጀው አንጸባራቂ ድል እንዳኮራውና በተቃራኒው አሸባሪው ቡድን በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት በዜጎች ህይወትና በንብረታቸው ላይ ያደረሰው ዝርፊያና ውድመት ደግሞ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ እንደሆነ ገልጿል።

የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ከተማዋን ለማውደም የፈፀሙት ጥፋት ሞራለቢሰነት የተሞላበት እንደሆነም አንስቷል።

የክፋት ሁሉ ባለቤት የሆነውን የህወሃት የሽብር ቡድንን ጥፋት የሚሰማና የሚመለከት የትግራይ ህዝብም በቃህ ሊለው እንደሚገባም አስገንዝቧል።

የሽብር ቡድኑን የጥፋት ጉዞ በመግታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ህዝቡ እያደረጉት ያለው አኩሪ ተጋድሎ የሚደነቅ እንደሆነም ገልጿል።

በ "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" ኢትዮጵያዊያን ሊሞቱ፣ ሊፈናቀሉና ሌሎች መስዋእትነቶችን ሊከፍሉ ይችላሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትሸነፍም ብሏል።

ወራሪው የህወሃት የሽብር ቡድን በጭፍራና ካሳጊታ ከተሞች ቤተ እምነቶችን በማውደም ቅዱስ ቁርዓንን ጨምሮ ሌሎች ቅዱሳት መጻህፍትን ማቃጠሉ እንዳሳዘነውም ጠቅሷል።

በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን በማካፈል፣ የወደሙ ቤተ እምነቶችንና መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በመድረስ ጉዳት የደረሰበትን ህዝብ መልሶ ማቋቋም ይገባል ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

በግንባር ተሰልፈው ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል የህይወት መስዋእትነት እየከፈሉ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን ከፍታ እንደሚያረጋግጡ ጥርጥር የለኝም ብሏል።  

ለሰራዊቱ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባም ገልጿል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በመደገፍ በየአውደ ግንባሩ እየተገኘ የአገር አለኝታነቱን በማረጋገጥ ላይ የሚገኝ ብርቅየ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም