የዞኑ ማህበረሰብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ465 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመትድጋፍ አደረገ

48

አምቦ፤ ህዳር 25/2014(ኢዜአ) የምዕራብ ሸዋ ዞን ማህበረሰብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ465 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ፡፡

በዞኑ በ22 ወረዳዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡

በዞኑ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር የመንግሥት ሰራተኞችን ጨምሮ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 465 ሚሊዮን 197ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሶምሳ እንዳሉት የዞኑ ማህበረሰብ ከጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ባሻገር 122 ሰንጋ  በሬዎች እና 80 በጎችና ፍየሎችን ድጋፍ አድርጓል።

አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ሀገር ለማፍረስ እየፈጸሙት ያለውን እኩይ ተግባር  ለማምከን የዞኑ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሯሯጡ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ አደብ እስኪገዙ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የዞኑ ወጣቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያን ለማዳን ወደ ግንባር በመዝመታቸው በከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ እንደሆኑም አስረድተዋል።

የአምቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ በቀለ ጫላ በሰጡት አስተያየት አሸባሪው ህወሓትና ተላላኪው ሸኔ ከድርጊታቸው እስኪታቀቡ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ጽጌረዳ ንጉሴ እንዳሉት "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ።

ከደንዲ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ በፍቃዱ ቱሉ በሰጡት አስተያየት ዘመቻው በአጠረ ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም