ወደ ቀያችን ተመልሰን በሽብር ቡድኑ የወደመችውን ከተማችንን ለመገንባት እንሰራለን

59

አዲስ አበባ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) ወደ ቀያችን ተመልሰን በአሸባሪው ህወሓት የወደመችውን ከተማችንን መልሰን ለመገንባት እንሰራለን፤ ሕይወትም ይቀጥላል ይላሉ የካሳጊታ ከተማ ነዋሪው አህመድ ሀሰን።

ካሳጊታ ከተማ ከአፋር ክልል መዲና ሰመራ በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።  

ከጭፍራ ጋር የሚያገናኝ ከ55 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም የጠጠር መንገድ ባለቤት በመሆኗ ከተማን ከከተማ፣ አፋር ክልልን ከአማራ ክልል በማገናኘት ለማኅበረሰብ የእርስ በእርስ ቅርርብ ጉልህ ፋይዳ አላት።

ካሳጊታ ወደ ባቲ፣ ኮምቦልቻና ደሴ የሚያልፉ ደንበኞቿ አረፍ ብለው ሻይ፣ ቡና እና ቁርስ የሚያደርጉባትም ነበረች።

በዚያ ያለው ማኅበረሰብም አንዱ በሻይ ቡና ሌላው በሱቅ እና በምግብ ቤት ስራዎች እርስ በእርሱ ተፈቃቅዶና ተከባብሮ የሚኖርባት የፍቅር ከተማ ነች ካሳጊታ።

ይሁንና አገር ለማፍረስ ከንቱ ውጥኑ እግሩ ደርሶ መዳረሻው ያደረጋት የሽብር ቡድኑ ህወሓት ወራሪ ለቀናት ቢቆይባት የተለመደ የጥፋትና የጭካኔ በትሩን ባገኘው ፍጥረትና ንብረት ሁሉ ላይ አሳርፎባታል።

ሞቃቷ ካሳጊታ በሽብር ቡድኑ ወራሪ የእብሪት ድርጊት የቀደመ ድምቀቷን ተገፋ በፍርስራሽና በቃጠሎ የተሞላች ሞገሷን ያጣች ከተማ ሆናለች።

የሽብር ቡድኑ በዚያ በቆየባቸው ቀናት መስጊድ፣ ቅዱስ ቁርዓን፣ ሱቅና ምግብ ቤቶችን ጨምሮ የሕዝብና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት እና መኖሪያ ቤቶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

እንደ ከተማዋ ነዋሪው አህመድ ሀሰን ገለፃ የአርብቶ አደር ንብረት የሆኑ የቤት እንስሳትን አርዶ መብላትና ገድሎ መሄድን ጨምሮ በርካታ ንጹኃንን በጥይትና በከባድ ድብደባ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ፈጽሟል ሽብርተኛው ወራሪ።

የንጹሃኑ አስከሬን ለቀናት እንዳይቀበር ማድረግም የሽብር ቡድኑ ወራሪ የቀን ተቀን ተግባራቸው እንደነበረም ያስታውሳሉ።

የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች በመከላከያ ሠራዊት፣ በአፋር ልዩ ኃይልና ሚኒሻ አኩሪ ተጋድሎ ተመትቶ መልቀቁ እፎይታ ሰጠን እንጂ በሰው ልጆች ላይ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ አሰቃቂ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ይቀጥሉ ነበር ነው ያሉት።

አቶ አህመድ አሁን የመኖሪያቸውን ካሳጊታን የቀድሞ ገጽታ ለመመለስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

እንደ አቶ አህመድ ሁሉ ታዳጊዋ ሃሊማ ሰይድም ተወልዳ ያደገችባት ከተማ ካሳጊታ ፈራርሳና ወድማ ማየቷ እንዳሳዘናት ገልፃለች።

አብሮ አደግ ጓደኞቿን ወደ ሰፈራቸው ተመልሰው ለማግኘት በጉጉት እየጠበቀቻቸው መሆኗንና ከተማቸውም በፊት ወደነበረችበት ትመለሳለች የሚል ተስፋ እንዳላት ገልጻለች።

ኢዜአ በካሳጊታ ባደረገው ምልከታ ወደ ቀያቸው በመመለስ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ኑሯቸውን እንደ አዲስ ለመጀመር እየሞከሩ መሆኑን አይቷል።

ይሁንና የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የጭካኔ ድርጊት፣ ሃብት ንብረታቸው መውደሙ፣ ጎረቤቶቻቸው መገደላቸው፤ የከተማዋ ወደ ፍርስራሽነት መቀየር የሃዘን ድባብ እንዲያጠላባቸው አድርጓቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም